ትምባሆን ለመከላከል የሚከናወኑ ተግባራት አካላዊና አካባቢያዊ ጤናችንን የሚያስጠበቁ ናቸው- ሲዲሲ አፍሪካ

96

ግንቦት 23 ቀን 2014(ኢዜአ)ትምባሆን ለመከላከል የሚከናወኑ ተግባራት አካላዊና አካባቢያዊ ጤናችንን የሚያስጠበቁ እጅግ ጠቃሚ ተግባራት ናቸው ሲል የአፍሪካ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል አስታወቀ።

የአፍሪካ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል ከባለድርሻ አካላት ጋር የአለም ጸረ ትምባሆ ቀንን “አለማችንን ለመታደግ ከትምባሆ ሱስ እንላቀቅ” በሚል መሪ ቃል አክብሯል።

ማዕከሉ ቀኑን አስመልክቶ ባስተላለፈው መልዕክት በትምባሆ ምክንያት በየአመቱ ከ8 ሚሊዮን በላይ ሰዎች እንደሚሞቱ ገልጿል።

በአፍሪካም የትምባሆ ምርትና የተጠቃሚዎች ቁጥር በየጊዜው መጨመሩ ጉዳዩን አሳሳቢ እንዳደረገው ያመለከተው ማዕከሉ እ.አ.አ ከ1980 እስከ 2016 ባሉት አመታት የትንባሆ ተጠቃሚዎች ቁጥር 52 በመቶ ማደጉን አብራርቷል።

በ2000 ዓ.ም የተጠቃሚዎቹ ቁጥር ከነበረበት 64 ሚሊዮን በ2018 ወደ 73 ሚሊዮን ማደጉንና በሁለተኛ ተጠቃሚነት በህዝባዊ ቦታዎች ትምባሆ ሳይፈልጉ የሚደርስባቸው አፍሪከውያን ቁጥርም የ48 ነጥብ 2 በመቶ ጭማሬ ማሳየቱን ገልጿል።

በሌላ በኩል ለትምባሆ ምርት የሚውሉ አካባቢዎች ላይ እንደ ደን ጭፍጨፋ፣ የበካይ ጋዝ ልቀት እና የምግብ ምርት እጥረት በማስከተል ለአስከፊ ጉዳቶች ይዳርጋል ሲል ሲዲሲ አሳስቧል።

ችግሩን ለመከላከል በዚህም አመት ትንባሆ ከግል ሕይወት ጀምሮ በአከባቢና አለማችን ላይ የሚደርሰውን ዘርፍ ብዙ ችግር ማሳወቅ እንዲሁም ጉዳቱን መቀነስ የሚያስቹሉ ተግባራት ቅድሚያ እንደተሰጣቸው ተነግሯል።

ትምባሆን ለመከላከል የሚከናወኑ ተግባራት አካላዊና አካባቢያዊ ጤናችንን የሚያስጠብቁ እጅግ ጠቃሚ ተግባራት ከመሆናቸውም በላይ የምንፈልጋትን አፍሪካ እውን ሆና ለማየት ያስችለናል ሲል አመልክቷል።

ለዚህም የአፍሪካ ህብረት አገራት የማዕከሉን የአምስት ዓመት ስትራቴጂያዊ እቅድ በወሰኑበት ሰነድ ለጤናማ አእምሮና በሽታን ለመከላከል በሚደረጉ ጥረቶች ትምባሆን መከላከል ከቀዳሚዎቹ ተግባራት መካከል መስፈሩን አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም