ቺሊ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በተለያዩ የትብብር መስኮች ለማጠናከር ትሰራለች

62

ግንቦት 23 ቀን 2014 (ኢዜአ) ቺሊ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በተለያዩ የትብብር መስኮች ለማጠናከር እንደምትሰራ በኢትዮጵያ የአገሪቱ አምባሳደር ፈርናንዶ ሳለኬት ተናገሩ።

አምባሳደር ፈርናንዶ ሳለኬት ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ቺሊና ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት የዘለቀ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አላቸው ብለዋል።

ሁለቱ አገራት አሁን ላይ በሕዝብ አስተዳደር፣ በትምህርት፣ በሳይንስና በሌሎች የልማትና ማኅበራዊ ዘርፎች ላይ በትብብር እየሰሩ መሆኑን ነው የጠቆሙት።

ቺሊ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ይህንን አጋርነት በተለያዩ የትብብር መስኮች ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላት ገልጸው፤ ለዚህም አገራቸው ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል።

በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የንግድና የኢንቨስትመንት ግንኙነት እንዲሁም በሳይንስ ዘርፍ ያለውን ትብብር ለማጠናከርም እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።  

በዚህም የአገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ እንደሚሰሩ አብራርተዋል።  

ቺሊ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ሊያጠናክሩ የሚችሉ መስኮችን በመለየት ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ትስስር ታጠናክራለችም ነው ያሉት።

ይህም የደቡብ ለደቡብ የሚደረገውን አጋርነት ለማጠናከር እንደሚያስችል ገልጸዋል።  

በደቡብ አሜሪካ ምስራቃዊ ክፍል የምትገኘው ቺሊ 20 ሚሊዮን የሚጠጋ የሕዝብ ብዛት አላት።

ቺሊ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፈጣን ምጣኔ ኃብታዊ እድገት በማስመዝገብ በድህነት ውስጥ የሚገኙ በርካታ ዜጎቿን ወደ መካከለኛ ገቢ ማስገባት ችላለች።

ቺሊ ከፍተኛ መጠን ያለው የመዳብ ማዕድን አምራች አገር ስትሆን የተለያዩ ማዕድናትና የግብርና ምርቶች ለውጭ ገበያ በማቅረብም ትታወቃለች።

የኢትዮጵያና ቺሊ ግንኙነት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1945 መጀመሩን መረጃዎች ያመላክታሉ።