ዩኒቨርሲቲው ከ3 ሺህ በላይ አዲስ ገቢ ተማሪዎችን ለመቀበል ተዘጋጅቷል

125

ጂንካ፤ ግንቦት 23/2014 (ኢዜአ)፡ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከ3 ሺህ በላይ አዲስ ገቢ ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቀ።

የጅንካ ዩኒቨርስቲ የፊታችን ግንቦት 25 እና 26/2014 ዓ.ም አዲስ ገቢ ተማሪዎችን ይቀበላል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ኩሴ ጉድሼ ዩኒቨርሲቲው 3 ሺህ 290 አዲስ ገቢ ተማሪዎችን ለመቀበል  ዝግጅቱን አጠናቋል።

ዩኒቨርሲቲው ዘንድሮ የሚቀበላቸው ተማሪዎች ቁጥር ባለፉት ዓመታት ከሚቀበላቸው ብልጫ ያለው መሆኑን አስረድተዋል።

ከጂንካ ከተማ ወጣቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎችና ሃይማኖት አባቶች ጋር በመሆን ለተማሪዎች አቀባበል እንደሚያደርግ ጠቁመው፤ በአርባ ምንጭና በኮንሶ ከተሞች የትራንስፖርት አገልግሎት ማመቻቸቱን ገልጸዋል።

ለተማሪዎቹ አገልግሎት የሚውሉ የመማሪያና የማደሪያ ክፍሎች የማስፋፊያ ግንባታ መከናወኑን ገልጸው፤ በውሃና የኤሌክትሪክ አገልግሎት ላይ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን ተናግረዋል።

የቤተ ሙከራና የቤተ መጻህፍት ክፍሎች ግብዓት ተሟልቶላቸው ለአገልግሎት ዝግጁ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ መምህራን እጥረት በታየባቸው የትምህርት ክፍሎች  ቅጥር መፈጸሙን ተናግረዋል። 

የጂንካ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ኅብረት ፕሬዚዳንት ናሆም ከፍያለው ነባር ተማሪዎች ትምህርታቸውን በሰላማዊ ሁኔታ እየተከታተሉ መሆናቸውን ገልጿል።

አዲስ ገቢ ተማሪዎችም ዩኒቨርሲቲው በመቀላቀል ያለ ምንም ስጋት ትምህርታቸውን እንዲከታተሉና በማህበራዊ ትስስር ገጾች ለሚናፈሱ ሀሰተኛ መረጃዎች ቦታ እንዳይሰጡ ጠይቋል።

ዩኒቨርሲቲውን የሚመለከት ትክክለኛ መረጃ ከዩኒቨርሲቲውና ከኅብረቱን የማህበራዊ ትስስር ገጾች ማግኘት እንደሚችሉም አመልክቷል።

 አዲስ ገቢ ተማሪዎችን  ለመቀበልና የተማሪ ወላጆች ያለምንም ስጋት ልጆቻቸውን ሸኝተው በሰላም እንዲመለሱ የሚያስችል ስራ መሰራቱን የተናገሩት ደግሞ የደቡብ ኦሞ ዞን  ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ደሞ በዛብህ ናቸው።

መምሪያው አዲስ ገቢ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲከታተሉ ለማስቻል የአካባቢውን ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ  ሃላፊነቱን እንደሚወጣ ተናግረዋል።

''ጂንካ በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች በፍቅር የሚኖሩባት የሰላም ተምሳሌት ናት'' ያሉት የከተማዋ ነዋሪ አቶ ሙሐመድ አሊ አዲስ ገቢ ተማሪዎችና ወላጆቻቸውን በኢትዮጵያዊ የእንግዳ አቀባበል ለማስተናገድ  መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

በ2010 ዓ.ም ከአንድ ሺህ ባልበለጡ ተማሪዎች የመማር ማስተማር ሥራ የጀመረው የጂንካ ዩኒቨርሲቲ አሁን ላይ  ከ6 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በመደበኛና በተከታታይ መርሐ ግብር ተቀብሎ በማስተማር ላይ እንደሚገኝ መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም