በደሴ የእሳት ቃጠሎ 6 ሰዎችን ሲጎዳ 31 ቤቶችን ደግሞ ሙሉ በሙሉ አወደመ

72

ግንቦት 23 ቀን 2014 (ኢዜአ)በደሴ ከተማ በተከሰተው የእሳት ቃጠሎ እስካሁን በተደረገው ማጣራት 6 ሰዎች ከመጎዳታቸው በተጨማሪ 31 የመኖሪያ እና የንግድ ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ መቃጠላቸውን ፖሊስ አረጋገጠ።

በደሴ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ 1ኛ ዋና ፖሊስ ጣቢያ ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ጥላሁን ፈንታው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ከሌሊቱ 6 ሰዓት ገደማ የተቀሰቀሰው የእሳት አደጋ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት አድርሷል፡፡

የእሳት አደጋው የተነሳበት አካባቢ አሮጌ እቃዎች የሚከማቹበትና ያረጁ ቤቶች ያሉበት በመሆኑ በቀላሉ ለማጥፋት ፈታኝ ቢሆንም በህብረተሰቡ ርብርብ እሳቱ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ሳይስፋፋ መቆጣጠር ተችሏል ብለዋል፡፡

ቃጠሎው ሊያጣራ የተቋቋመው ኮሚቴ እስካሁን እሳቱን በማጥፋት ላይ ከነበሩ ሰዎች መካከል በ6 ሰዎች ላይ ቀላልና ከባድ ጉዳት መድረሱን አረጋግጠናል ብለዋል፡፡

የተጎዱ ሰዎች ቁጥር እንደሚጨምር ጠቁመው ተጎጅዎች በደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይድ ሆስፒታል ህክምና እያገኙ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም እስካሁን በተደረገው ማጣራት 24 መኖሪያ፣7 የንግድና ድርጅት ቤቶች ከእነ ሙሉ ንብረታቸው ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን ተናግረዋል፡፡

እንደ ኃላፊው ገለጻ የአሮጌ እቃ ማከማቻ ቤትም አብሮ የወደመ ሲሆን የቃጠሎው ፍንጥርጣሪ ሸዋ ብር መስጅድን ጨምሮ በተወሰነ ርቀት ላይ የሚገኙ መኖሪያ ቤቶችንና ተቋማት ላይም መጠነኛ ጉዳት አድርሷል።

ጉዳዩ ውስብስብና ጥንቃቄ የሚሻ ቢሆንም መንስኤውና እንዴት ለሚለው ጥያቄ መልስ ለመስጠት በቅንጅት አሁንም እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

አሁን ላይ ተጎጅዎችን የማረጋጋት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው አጠቃላይ የደረሰውን ውድመትም ለህዝብ እንደሚያደርሱ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም