የሲቪክ ማህበራት ድርጅቶች የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥና መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

141

አዳማ፣ ግንቦት 23 ቀን 2014 (ኢዜአ) የሲቪክ ማህበራት ድርጅቶች የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥና መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን የድርሻቸውን እንዲወጡ የኢትዮጵያ ህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ጠየቀ።

ተቋሙ ብዙሃንና የሲቪክ ማህበራት ብልሹ አሰራርን በመታገልና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት ውስጥ ሚናቸውን እንዲወጡ ለማስቻል ያለመ መድረክ በአዳማ ከተማ እያካሄደ ነው።

ዋና ዕንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ሃይሌ በመድረኩ እንደገለፁት፤ የህግና የመልካም አስተዳደር ጥሰት እንዳይፈፀም ተቋማቱ ሚናቸውን ለመወጣት በቂ እንቅስቃሴ እያደረጉ አይደለም።

በመሆኑም ህዝብ ብሶት የሚያሰማባቸው የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ ብዙሃንና የሲቪክ ማህበራት አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

May be an image of 1 person and standing

ዴሞክራሲ እንዲጎለብትና የተሻለ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስነ ምህዳር እንዲፈጠር ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ መስራት እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል።

በመንግስት መዋቅር ውስጥ የሚታዩ ብልሹ አሰራሮች እንዲወገዱ በትብብር ከመስራት ይልቅ በተናጥል በመንቀሳቀሳችን የተፈለገውን ውጤት እንዳናመጣ አድርጎናል ብለዋል።

የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በበኩላቸው ከለውጡ ወዲህ የማህበራቱን በአዲስ መልክ ከማደራጀት ጀምሮ የማንቃት ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።

በዚህም የብዙሃንና የሲቪክ ማህበራት ራሳቸውን ቀደም ሲል ከነበራቸው ቁመና በተሻለ ማደራጀታቸውን ገልጸው፤ ነገር ግን የህግና መልካም አስተዳደር ጥሰት፣ በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ላይ ያላቸው አስተዋጽኦ ብዙ እንደሚቀረው ጠቁመዋል።

የብዙሃንንና የሲቪክ ማህበራት ድርጅቶች የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማስቻል መንግስት አሰራሮችና ህጎችን ከማሻሻል ጀምሮ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ማከናወኑን አመልክተው፤ ድርጅቶቹ በማንኛውም ህጋዊ ጉዳዮች እንዲሳተፉ መፍቀዱ ትልቅ ለውጥ ነው ብለዋል።

በሙሉ አቅማቸው እንዲሰሩ መንግስት እያበረታታ ነው ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ ድርጅቶችን ለመደገፍና ለማገዝ በተለይ ማህበራቱ ከለጋሾች ጥገኝነት እንዲላቀቁና የራሳቸውን ገቢ ማመንጨት እንዲችሉ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በዴሞክራሲ ስርዓትና ሀገረ መንግስት ግንባታ የድርሻችንን ከማበርከት ባለፈ የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ፣ ብልሹ አሰራር እንዲወገድና የመልካም አስተዳደር ጥሰት እንዳይፈፀም መስራት አለብን ብለዋል።

የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ የብዙሃንና የሲቪክ ማህበራት ተቋማት በትብብር መስራት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም