በደሴ ከተማ በድርጅትና መኖሪያ ቤቶች አካባቢ የተከሰተ የእሳት አደጋ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱን ፖሊስ ገለጸ

170

ደሴ፣ ግንቦት 23 ቀን 2014 (ኢዜአ) በደሴ ከተማ አስተዳደር በተለምዶ አራዳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በድርጅትና መኖሪያ ቤቶች አካባቢ የተከሰተ የእሳት አደጋ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱን ፖሊስ ገለጸ፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ መምሪያ የአንደኛ ፖሊስ ጣቢያ ኃላፊ ኢንስፔክተር ጥላሁን ፈንታው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ከለሊቱ 6 ሰዓት ገደማ የተቀሰቀሰውን የእሳት አደጋ ለመቆጣጠር ርብርብ ሲያደርጉ በነበሩ ሰዎች ላይም ጉዳት አስከትሏል።

ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በሰዓቱ ወደ ህክምና ተቋም ሄደው እርዳታ እንዲያገኙ እንደተደረገም ተናግረዋል።

“የእሳት አደጋው የተነሳበት አካባቢ አሮጌ እቃዎች የሚከማቹበትና ያረጁ ቤቶች ያሉበት በመሆኑ በቀላሉ ለማጥፋት ፈታኝ ቢሆንም በህብረተሰቡ ርብርብ እሳቱ ሳይስፋፋ መቆጣጠር ተችሏል” ብለዋል፡፡

የእሳት አደጋ ማጥፊያ ተሸከርካሪ ከኮምቦልቻ ከተማ ጭምር መጥቶ ለማጥፋት ርብርብ መደረጉን ጠቁመው፤ በቅንጅት አደጋው የከፋ ጉዳት ሳያስከትል በቁጥጥር ስር መዋሉን ገልጸዋል።

የአደጋው መንስኤ፣ የደረሰውን አጠቃላይ ጉዳት፣ የተቃጠሉ ቤቶችና ሌሎችንም የሚያጣራ ቡድን ወደ ቦታው ተልኮ ስራ መጀመሩን ኃላፊው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም