በደብረብርሃን ከተማ ለሚገኙ ተፈናቃዮችና ትምህርት ተቋማት ከ11ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

123

ደብረ ብርሀን፤ ግንቦት 22/2014 (ኢዜአ) ሕይወት ኢትዮጵያ የተባለ በጎ አድራጎት ድርጅት በአሸባሪዎቹ ህወሓት እና ሸኔ ተፈናቅለው በደብረ ብርሃን ከተማ ጊዜያዊ መጠለያ ለሚገኙ ወገኖችና ለተጎዱ የትምህርት ተቋማት ከ11 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

የህይወት ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር እና የአስቸኳይ ጊዜ የአደጋ ምላሽ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ጌታለም ካሳ በርክክብ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት፣ ድርጅታቸው በጦርነቱ ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖችና ለተዘረፉ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት  የበኩሉን ድጋፍ እያደረገ ነው።

11 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚገመተው ድጋፍ የተገኘው ድርጅቱ ከ''ማላላ ፈንድ'' ጋር በመተባበር በተቀረጸ የትምህርት ዘርፍ የአደጋ ጊዜ ምላሽ ፕሮጀክት መሰረት መሆኑንም ገልጸዋል።

በእዚህም በደብረ ብርሃን፣ በደብረሲና፣ በሸዋሮቢት፣ በአጣየ እና በኤፍራታና ግድም ወረዳ ባሉ 4 መጠለያ ጣቢያዎችና ከመጠለያ ጣቢያው ውጪ ላሉ የማህበረሰብ ክፍሎች የምግብ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።  

በእዚህም 100 ካርቶን ፓስታ፣ 750 ሊትር የምግብ ዘይት፣ 100 ኩንታል ዱቄት፣ 100 የለሊት አልባሳት፣ 100 ፍራሽና ሌሎች የንጽህና መጠበቂያ ቁሶችን ድጋፍ ማድረጉን አመልክተዋል።

ከእዚህ በተጨማሪ በዞኑ በጦርነቱ በሸዋሮቢት፣ ኤፍራታና ግድም ወረዳ እንዲሁም በአጣየ ከተማ ላሉ 6 ትምህርት ቤቶች የተማሪ መቀመጫ ወንበሮችና  ጥቁር ሰሌዳዎችን እያሟላ መሆኑን ተናግረዋል።

ለ1ሺህ 800 ተማሪዎችም የትምህርት ቤት የደንብ ልብስ፣ ደብተር፣ ብዕርና ሌሎች አስፈላጊ ቁሶችን እየደገፈ መሆኑን አመልክተው፤ ለ1 ሺህ 200 ልጃገረድ ተማሪዎች የንጽህና መጠበቂያ ድጋፍ  መደረጉን ተናግረዋል።

በድጋፍ ርክክቡ ላይ የተገኙት የሰሜን ሸዋ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ ደረጀ ይንገሱ በበኩላቸው፣ በሰላም እጦት ምክንያት ከቀያቸው ተፈናቅለው በማህበረሰቡ ውስጥና በጊዜያዊ መጠለያ ከ50 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች እንዳሉ ገልጸዋል።

ድርጅቱ ያደረገው ድጋፍ ከእለት ጉርስና አልባሳት ባሻገር ዘላቂ በሆነ የትምህርት ዘርፍ ላይ ያተኮረ ጭምር በመሆኑ ጠቀሜታው የጎላ  ነው ብለዋል።

የዞኑ ትምህርት መምሪያ ሃላፊ አቶ ወሰን ለገሰ በበኩላቸው፣ አሸባሪው ህወሓት በ185 የትምህርት ተቋማት ላይ ጉዳት መድረሱን አስታወሰዋል።

በዚህም 127 ሚሊዮን ብር የሚገመት የትምህርት ቁሳቁስ መውደሙንና 180 ሺህ ተማሪዎች ለችግር መጋለጣቸውን አመልክተዋል።

ከተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ደርጅቶች በተገኘ ድጋፍ ተማሪዎች  ወደ ትምህርት ቤት ገበታቸው  እንዲመለሱ መደረጉን ተናግረዋል።

ድርጅቱ ዛሬ ያደረገው ድጋፍ የመማር ማስተማር ሂደቱን እንደሚያጠናክረው ገልጸው፤ ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም