የዓለም አካባቢ ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ በአዲስ አበባና በጅግጅጋ ከተሞች በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል

65

ግንቦት 22 ቀን 2014 (ኢዜአ) የዓለም አካባቢ ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ በአዲስ አበባና በጅግጅጋ ከተሞች በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን አስታወቀ።

የዓለም የአካባቢ ቀን “አንድ ምድር ብቻ” በሚል መሪ ሃሳብ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ50ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ29ኛ ጊዜ ይከበራል፡፡

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታሁን ጋረደው ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ቀኑ በአገር አቀፍ ደረጃ  ከሰኔ 2 እስከ 6  ቀን 2014 ዓ.ም በአዲስ አበባና ጅግጅጋ ከተሞች እንደሚከበር ገልጸዋል፡፡

በዚህም በኤግዚቢሽንና በፓናል ውይይቶች እንዲሁም የልምድ መለዋወጫ መድረኮች እንደሚዘጋጁም ነው የጠቆሙት፡፡

ቴክኖሎጂን በመጠቀም የአካባቢን ጉዳት በሚቀንሱ ተግባራትን የሚያከናውኑ አካላት የሚሳተፉበት ኤግዚቢሽን ከግንቦት 26 እስከ 29 ቀን 2014 ዓ.ም በወዳጅነት ፓርክ እንደሚካሄድም አመልክተዋል።

በአዲስ አበባና በጅግጅጋ ከተማ የፓናል ውይይት እንደሚከናወን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በውይይቱም  ዩኒቨርስቲዎች፣የልማት አጋሮች፣ የምርምር እንዲሁም በአካባቢና የአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚሰሩ ተቋማት እንደሚሳተፉ ገልጸዋል፡፡

በጅግጅጋ ከተማ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የስፖርት እና የጥያቄና መልስ ውድድር እንደሚካሄድም እንዲሁ።  

በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበረውን የ2022 የዓለም የአካባቢ ቀን የስዊድን መንግሥት ከተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም  ጋር በመተባበር እንደሚያስተናግድም ተገልጿል፡፡

የዘንድረው የዓለም አካባቢ ቀን መሪ ሃሳብ “አንድ ምድር ብቻ”  ሲሆን፤ ይህም  "ከተፈጥሮ ጋር ተስማምቶ በዘላቂነት መኖር” የሚል መልዕክት እንደሚያስተላልፍ ተጠቁሟል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1972 በስዊድን ስቶክሆልም ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ የዓለም የአካባቢ ቀን በየዓመቱ ግንቦት 28 እንዲከበር መወሰኑ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም