በግጭትና በተፈጥሮ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የማኅበራዊ ድጋፍ አገልግሎት ለሚሰጡ ባለሙያዎች ሥልጠና እየተሰጠ ነው

80

አዲስ አበባ ግንቦት 22/9/2014 /ኢዜአ/ በግጭትና በተፈጥሮ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የሥነ-ልቦናና ሌሎች የማኅበራዊ ድጋፍ አገልግሎት ለሚሰጡ ባለሙያዎች የሦስት ቀናት ሥልጠና በደብረ ብርሃን ከተማ ተጀመረ።

ሥልጠናው በማኅበራዊ፤ በጤና፣ በትምህርትና በሌሎች ዘርፎች የተሰማሩ 300 ባለሙያዎችን ተሳታፊ ያደርጋል ተብሏል።  

ሥልጠናው በቀጣይም በኮምቦልቻ፣ በወልዲያና በሰቆጣ ከተሞች የሚሰጥ ሲሆን በድምሩ 1 ሺህ 200 ሰልጣኞች ይሳተፋሉም ነው የተባለው።  

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ፤ በአገሪቷ በተፈጠሩ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ምክንያት በርካታ ሰዎች ለተለያዩ ችግሮች ተጋልጠዋል ብለዋል።

የተፈጠሩ አደጋዎች በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ብቻ ሳይሆን በሕዝቡ የአእምሮ ጤና፣ ሥነ-ልቦናዊና በማኅበራዊ ሕይወታቸው ቀላል የማይባል ተፅእኖ አሳድሯል ነው ያሉት።

ይህንንም ለመቅረፍ ሚንስቴሩ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የአእምሮዊ ጤና፣ የሥነ-ልቦናና የማኅበራዊ አገልግሎት እገዛ ለሚያደርጉ አካላት ለሦስት ቀናት የሚቆይ የአሰልጣኞች ሥልጠና በዛሬው ዕለት መጀመሩን ገልፀዋል።

ሠልጣኞች ያገኙትን ሥልጠና ተጠቅመው በሰው ሰራሽ እንዲሁም በተፈጥሮ አደጋ ተፅዕኖ የደረሰባቸውን ወገኖች የሥነ-ልቦና ብሎም የማኅበራዊ አገልግሎት እገዛ እንዲያደርጉ ያግዛል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም