ኦሊምፒክ ከውድድር ባለፈ የሰላም፣ የአብሮነትና የወንድማማችነት ማጠናከሪያ መድረክ ነው

41

ግንቦት 21/2014/ኢዜአ/ ኦሊምፒክ ከውድድር ባለፈ የሰላም፣ የአብሮነትና የወንድማማችነት ማጠናከሪያ መድረክ መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።

የመጀመሪያው ሀገር አቀፍ የወጣቶች ኦሎምፒክ ውድድር በሲዳማ ክልል አስተናጋጅነት በሀዋሳ ከተማ ተጀምሯል።

በመክፈቻው የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞን ጨምሮ በርካታ ታዳሚዎች ተገኝተዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ መልእክት ያስተላለፉት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፤ ኦሊምፒክ ከውድድር ባለፈ የሰላም፣ የአብሮነትና ወንድማማችነት ማጠናከሪያ መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ታሪክ ከጀግናው አትሌት አበበ ቢቂላ አሸናፊነት እና ድል አድራጊነት ጀምሮ  በትውልድ ቅብብሎሽ እስካሁን መቀጠሉን ገልጸዋል።

በመሆኑም የኦሊምፒክ መድረክ ከውድድር ባለፈ የአገር ግንባታ መሰረት፣ የሰላምና አብሮነት ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በሲዳማ ክልል አስተናጋጅነት እየተካሄደ ያለው የመጀመሪያው ሀገር አቀፍ የወጣቶች ኦሎምፒክ በርካታ ነገሮችን በመጋራት የአብሮነት እሴቶቻችን የሚጎለብቱበት ልዩ አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም በውደድሩ በስፖርታዊ ጨዋነት በመፎካከር ለሰላም፣ ፍቅርና አብሮነት በጋራ መቆማችሁን በተግባር ማሳየት አለባችሁ ብለዋል።

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ፤ ኦሊምፒክ የዘር የኋይማኖት የፆታ ልዩነት ሳይለይ በጋራ የሚያሰባስብ የአብሮነት መድረክ መሆኑን ጠቅሰዋል።

እንግዶች አጠቃላይ ተወዳዳሪዎች በሀዋሳ የሚኖራቸው ቆይታ ያማረና በውድድሩም መልካም እንዲገጥማቸው ተመኝተዋል።

በሲዳማ ክልል አስተናጋጅነት በሚካሄደው የመጀመሪያው ሀገር አቀፍ የወጣቶች ኦሎምፒክ ውድድር በአትሌቲክስ እግር ኳስ እና ሌሎችንም ጨምሮ ከ12 በሚበልጡ የስፖርት አይነቶች ውድድር ይካሄዳል።

በውድድሩ ከተለያዩ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ከ4 ሺህ በላይ ስፖርተኞች የተሳተፉ ሲሆን ከዛሬ ጀምሮ እስከ ሰኔ 4  ቀን 2014 ዓ.ም ይካሄዳል።