በአማራ ክልል በእርሻ ኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩ ብዙዎቹ ባለሃብቶች ከአርሶ አደሩ አቅም በታች እያመረቱ እንደሆነ ተጠቆመ

221

ባህርዳር፣ ግንቦት 21 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል ውስጥ በእርሻ ኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩ ብዙዎቹ ባለሃብቶች ከአርሶ አደሩ አቅም በታች እያመረቱ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው በግብርና ልማት ዘርፍ በክልሉ ከተሰማሩ ባለሃብቶች ጋር በ2014/2015 የምርት ዘመን ላይ ያተኮረ ውይይትም በባህርዳር አካሂዷል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አጀበ ስንሻው በውይይት መድረኩ ላይ እንደተናገሩት፤ በክልሉ 1 ሺህ 483 ባለሃብቶች በእርሻ ኢንቨስትመንት ዘርፍ ፈቃድ ወስደዋል።

ከ190 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለእርሻ ኢንቨስትመንት አገልግሎት ለባለሃብቶቹ ቢተላለፍም የሚያመርቱት ምርት አርሶ አደሩ ከሚያመርተው ያነሰ እንደሆነ ጠቁመዋል።

አብዛኛው ባለሃብት በአህያና በበሬ የሚያርስና በሄክታር 15 ኪሎ ግራም ማዳበሪያ ብቻ የሚጠቀም በመሆኑ ምርታማነቱ ዝቅተኛ መሆኑን ተናግረዋል።አርሶ አደሩ በሄክታር በአማካኝ ከ24 ኩንታል በላይ ምርት እያመረተ መሆኑን ጠቅሰው፤ ባለሃብቶቹ የሚያመርቱት ምርት በሄክታር በአማካኝ ከ20 ኩንታል አይበልጥም ብለዋል።የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ ባለሃብቶቹ በገቡት ውል መሰረት በቴክኖሎጂ ታግዘው በማልማት ለአርሶ አደሩ ምሳሌ ሊሆኑ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ኃይለማርያም ከፍያለው በበኩላቸው ባለሃብቶቹ በቴክኖሎጂ ታግዘው ማልማት ከቻሉ ምርታማነትን በሚፈለገው ደረጃ ማሳደግ እንደሚቻል ገልጸዋል።

ባለሃብቶቹ የወሰዱትን መሬት በውላቸው መሰረት በቴክኖሎጂ ታግዘው ማልማት ካልቻሉ ውሉ እንደሚቋረጥ አስጠንቅቀው፤ መሬቱ የተሻለ ለሚያለማ ባለሃብት እንደሚተላለፍ ጠቁመዋል።

ክልሉ በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሃብቶች አስፈላጊውን እገዛ ለማድረግ ዝግጁ እንደሆነ በመጥቀስ።

በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሃብቶች በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት የወሰዱት መሬት ጦም እንዳያድርም በቻሉት ልክ ለማልማት ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

በአንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋለው የሰላም እጦትና የሰው ማገት ችግር እንዲሁም የመካናይዜሽንና የምርጥ ዘር አቅርቦት እጥረት እንዲፈታላቸው ጠይቀዋል።

ክልሉ የትራክተር ችግራቸውን በመፍታቱ በቀጣይ የተሻለ አልምተው ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እንደሚሰሩም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም