የጠብታ መስኖ ቴክኖሎጂ ድካም ቀንሶ፣ ጊዜና ውሃን ቆጥቦ አርሶ አደሮችን የተሻለ አምራች እያደረገ ነው

215

ግንቦት 21/2014/ኢዜአ/ የጠብታ መስኖ ቴክኖሎጂ ድካም ቀንሶ፣ ጊዜና ውሃን ቆጥቦ የተሻለ አምራች እያደረጋቸው መሆኑን በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ አርሶ አደሮች ገለጹ።

የሸንኮራ ወንዝ በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ሶስት ቀበሌዎችን በመስኖ ተጠቃሚ ቢያደርግም የውሃ መጠኑ እና የመስኖ አልሚዎች ቁጥር ተመጣጣኝ አይደለም።

በአካባቢው ያጋጠመውን የውሃ እጥረት ተከትሎ 'ቴክኖሰርቭ ኢትዮጵያ' በተሰኘ ድርጅት ድጋፍ ወረዳው ለመጀመሪያ ጊዜ የጠብታ መስኖ ቴክኖሎጂን ተግባራዊ ማድረግ ችሏል።

በዚሁ ቴክኖሎጂ የውሃ እጥረት ባለባቸው ሶስት ቀበሌዎች ላይ በስምንት ሄክታር መሬት ላይ በሽንኩርት ሰብል ተሞክሮ ውጤታማ መሆኑን በወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት የመስኖ አግሮ-ኢኮኖሚ ባለሙያው ሰናይ ለገሰ ይናገራሉ።

የጠብታ መስኖ ቴክኖሎጂ 97 በመቶ ውሃን የመቆጠብ አቅም ያለው ሲሆን በሰው ሃይል ቅነሳ፣ በጊዜ ቁጠባና በሰብል እንክብካቤ አዋጭ መሆኑ ተመልክቷል።

ቴክኖሎጂው የአፈር ጨዋማነትና አሲዳማነትን በመቀነስ፣ አረም እንዳይበቅል በማድረግና በሌሎችም ጠቃሚ ምክንያቶች ተመራጭ መሆኑን ባለሙያው ጠቅሰዋል።

የጠብታ መስኖ ቴክኖሎጂ አዲስ በመሆኑ አሁን ላይ በርካታ አርሶ አደሮችን ማሳተፍ እንዳልቻለ ጠቅሰው በቀጣይ ብዙዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን ገልጸዋል።

በኢራንቡቱ ቀበሌ በጠብታ መስኖ ሽንኩርት ልማት እያከናወኑ ካሉ አርሶ አደሮች መካከል ያነጋገርናቸው አልሚዎች የጠብታ የመስኖ ቴክኖሎጂ ድካም ቀንሶ፣ ውሃ ቆጥቦ፣ አረም አስወግዶ የተሻለ አምራች አድርጎናል ብለዋል።

አርሶ አደር በለጠ ስዩም እና ኢዮብ ከፋለ ቴክኖሎጂው የውሃ እጥረትን ከማቃለሉ ባሻገር በሰው ሃይል፣ በግብዓት ፍጆታ፣ ወጭ በመቆጠብ፣ በሰብል እንክብካቤ ምቹ ሲሆን በምርታማነቱም የተሻለ ሆኖ አግኝተነዋል ብለዋል።

በእስራኤል እንደተጀመረ የሚነገርለት የጠብታ መስኖ የተጠራቀመ ውሃን በፕላስቲክ ቱቦ በማሰራጨት የተዘራን ሰብል በተመሳሳይ ሰዓት እኩል የውሃ ጠብታ እንዲያገኝ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም