የኢትዮጵያን ዘመን ተሻጋሪ ታሪኮችና የካበቱ ባህሎች የአንድነታችን መሰረት በማድረግ ልንጠቀምባቸው ይገባል

160

ግንቦት 21/2014/ኢዜአ/የኢትዮጵያን ዘመን ተሻጋሪ ታሪኮችና የካበቱ ባህሎች የአንድነታችን መሰረት በማድረግ ልንጠቀምባቸው ይገባል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የታሪክ ምሁራን ገለጹ።

ኢትዮጵያ ከአድዋ የድል ታሪክ እስከ አፍሪካ አንድነት ምስረታ ሂደት የሚሪነት ሚና በመጫዎት በብዙ መልኩ ትወደሳለች።

የሰው ልጅ የተገኘባት እና ቡና የበቀላባት ምድር በመሆኗ ከራሷ አልፎ ለዓለም የሚሻገር የታሪክ ባለቤት መሆኗም ይታወቃል።

የባህል፣ የማንነት፣ የቋንቋ፣ የእምነት እና ሌሎች ልዩነቶችም የኢትዮጵያ ውበትና የልዩ መገለጫ ምልክቶች ሆነው ቀጥለዋል።

በመሆኑም እነዚህንና ሌሎች የኢትዮጵያን ዘመን ተሻጋሪ ታሪኮችና የካበቱ ባህሎችን የአንድነታችን መሰረት በማድረግ ልንጠቀምባቸው እንደሚገባ የታሪክ ምሁራን ይናገራሉ።

ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ሁለንተናዊ እድገት መሰረት የሚያጸና አካታች፣ አሳታፊ እና ገለልተኛ አገራዊ ምክክር ጥሩ መሰረት የሚያኖሩ በርካታ እሴቶች መኖራቸውንም ጠቅሰዋል።  

በባህር-ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህርና የታሪክ ኢምሬትስ ፕሮፌሰር ሹመት ሲሻኝ፤ የኢትዮጵያ ጥልቅና ድንቅ ታሪኮችና የተለያዩ እሴቶች የጋራ ሃብትና የአንድነት መሰረቶች መሆናቸውን ይናገራሉ።

በመሆኑም እነዚህን መልከ ብዙ መገለጫዎችና ከአገርም የተራመዱ ታሪኮች ለኢትዮጵያ ጽኑ መሰረት ግንባታ ግብአት ልናውላቸው ይገባል ብለዋል።

በዲላ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ረዳት ፕሮፌሰር አብዱ መሀመድ፤ ለአገራዊ የምክክር ሂደቱ ስኬት በተቃርኖ ከሚያቆሙን ጥቂት ነገሮች ይልቅ አንድ በሚያደርጉን የጋራ እሴቶቻችን ላይ በማተኮር በጋራ መስራት አለብን ብለዋል።

አገራዊ የምከክር ሂደቱ ብሄራዊ መግባባትና እርቅን ለመፍጠር የማይተካ ሚና እንዳለው ጠቅሰው አጋጣሚውን ልንጠቀምበት ይገባል ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ሂደት 11 ኮሚሽነሮች ተሰይመውለት ሁሉን አቀፍ የምክክር መድረክ ለመፍጠር ስራ መጀመሩ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም