የኢትዮ-ጂቡቲ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች በአፋር ክልል የሚገጥማቸውን ችግር ለመፍታት እየተሰራ ነው

234

ግንቦት 21 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮ-ጂቡቲ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች በአፋር ክልል የሚገጥማቸውን ችግር ለመፍታት ክልሉ ከፌዴራል መንግስት ጋር በመተባበር እየሰራ መሆኑን ገለጸ።

የክልሉ መንገድ ልማትና ትራንስፖርት ቢሮ የኢትዮ-ጂቡቲ ከባድ መኪና አሸከርካሪዎች በክልሉ የጸጥታና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እያጋጠሟቸው እንደሆነ ማረጋገጡን ገልጿል።

ችግሩን ለመፍታት በየደረጃዉ ከሚመለከታቸዉ የክልልና የፌዴራል አካላት ጋር በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

የኢትዮ-ጂቡቲ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ከክልሉ መንገድ ልማትና ትራንስፖርት ቢሮ በሰመራ-ሎግያ ከተማ ባደረጉት ውይይት በክልሉ ችግር እየገጠማቸዉ መሆኑን ገልጸዋል።

በውይይቱ ከተሳተፉት አሽከርካሪዎች መካከል አቶ ታደሰ ለማ እንደተናገሩት፤ በተለይም ከእንድፎ እስከ ሚሌ ድረስ ባለዉ መስመር ብዙ ጊዜ መሳሪያ የታጠቁ ሰዎች መንገድ በመዝጋት ዝርፊያና ተያያዥ ወንጀል እንደሚፈጽሙ ተናግረዋል።

May be an image of 6 people, people sitting and people standing

“ከዚህ ባለፈም ብዙ ጓደኞቻቸዉ በአካባቢው ከታጣቂዎች በሚተኮስ ጥይት ህይወታቸን አጥተዋል” ሲሉ ተናግረው፤ የሚመለከተዉ አካል በስርአት አልበኞች አሽከርካሪዎች ላይ የተደቀነውን የደህንነት ስጋት መግታት እንደሚገባ ገልጸዋል።

ሌላዉ አሽከርካሪ ታምራት ከበደ በበኩላቸው የጸጥታ ቁጥጥር በተለያዩ ምክንያቶች በመላላቱ መንገዱ ፈታኝ እየሆነ መምጣቱን አመልክተዋል።

“በየከተማዉ የመንገድ ትራንስፖርት ተቆጣጣሪዎች ነን የሚሉ ሰዎች ህጋዊነታቸዉን የሚገልጽ ምንም አይነት መለያ ሳያደርጉ እንደሚያጉላሏቸውና አካላዊ ጥቃት እያደረሱብን ነው” ብለዋል።

ከአዋሽ እስከጋላፊ ድረስ ሲጓዙ በየመንገዱ በሚገኙ የመንገድ ትራንስፖርት ተቆጣጣሪዎችም ሆነ ትራፊክ ፖሊሶች የእጅ መንሻ በግልጽ እንደሚጠይቁ የገለጹት አሽከርካሪ ካሚል አብደላ ናቸው።

ችግሩ ከአቅም በላይ በመሆኑ መንግስት ተከታትሎ እነዚህን አካሎች ስርአት እንዲያሲዛቸው ጠይቀዋል።

በክልሉ መንገድ ልማትና ትራንስፖርት ቢሮ የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ስምሪት ዳይሬክተር ሁሴን ቦሎኮ የከባድ መኪና አሸከርካሪዎች ህይወታቸዉን ለአደጋ ሰጥተዉ ወገናቸውን እያገለገሉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

May be an image of 4 people, people sitting, people standing and indoor

የአሽከርካሪዎቹ ደህንነትና ሰላም መረጋገጥ ከሀገር ሰላምና ደህንነት ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተቆራኘ በመሆኑ የክልሉ መንግስት ሃላፊነቱን በብቃት እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።

ከአሽከርካሪዎቹ የተነሱት ችግሮች መኖራቸውን ገልጸዉ፤ ችግሮቹን ለመፍታት ከሚመለከታቸዉ ባለድርሻዎች ጋር በመሆን በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም የመንገድ ተቆጣጣሪዎች በከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ላይ የሚፈጥሩት መጉላላትና እንግልት ለማስቀረት ተቆጣጣሪዎቹ ከባድ መኪና እንዳያስቆሙ ትእዛዝ ተላልፏል ብለዋል።

May be an image of outdoors and text that says "SCANIA"
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም