ቢሮው በጦርነትና በድርቅ ጉዳት የደረሰባቸዉን ወገኖች ለመደገፍ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ

98

ደብረብርሃን፣ ግንቦት 21 ቀን 2014 (ኢዜአ) በጦርነትና በድርቅ ጉዳት የደረሰባቸዉን ወገኖች ለመደገፍ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ቢሮ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

ቢሮው ከክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ጋር በመተባበር በአማራ ክልል በአጣየ ከተማ በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች 800 ሺህ ብር ግምት ያለው የቁሳቁስ ድጋፍ ዛሬ አድርጓል።

የቢሮው ኃላፊ  ወይዘሪት ለምለም አምሳሉ በድጋፍ ርክክቡ ወቅት እንደገለጹት፤ በጦርነቱና በድርቅ አደጋ ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን ከመቸውም ጊዜ በበለጠ መደገፍ ያስፈልጋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ጉዳት የደረሰባቸዉን ወገኖች በዘላቂነት ለመደገፍ አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

አሁን የማብሰያና የመመገቢያ ቁሳቁስ ድጋፍ በ800 ሺህ ብር ወጪ ድጋፍ መደረጉን የገለጹት ወይዘሪት ለምለም፤ በቀጣይም የክልሉን ህዝብ በማስተባበር በሌሎች አካባቢዎች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

በፌዴራል ብልጽግና ፓርቲ የሴቶች ሊግ አደረጃጀት ዘርፍ ሀላፊ ወይዘሮ አሰለፈች ታደሰ በበኩላቸዉ አንድ እቃ ለአንድ ተፈናቃይ እና 200 ብር ለእናቴ በሚል የ100 ሚሊዮን ብር እቃዎችን በማሰባሰብ ለተጎጅዎች ማድረስ መጀመሩን ተናግረዋል።

የዛሬዉ ድጋፍም የዚህ አካል መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይም ድጋፉ በሌሎች አካባቢዎች በጦርነትና በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የማሰራጨቱ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስረድተዋል።

የተደረገው የቁሳቁስ ድጋፍ ለተጎዱ ወገኖች ልዩ ትርጉም አለዉ ያሉት ደግሞ በአማራ ክልል የብልፅግና ፓርቲ የሴቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ምክትል ሀላፊ ወይዘሮ እሌኒ አባይ ናቸው።

ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበው፤ የተፈናቀሉ ዜጎች ራሳቸውን እስኪችሉ ድረስ የተጀመረው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል።

የአጣየ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ፀጋየ ጣሰዉ የተደረገው ድጋፍ ቤት ንብረታቸዉ ወድሞ በጊዜያዊ መጠለያ ለሚገኙ ሴቶች በፍትሃዊነት እንደሚሰራጭ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም