“የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለአዲስ አበባ ወጣቶች የአንድነት ማሳያ ነው” – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

54

ግንቦት 21 ቀን 2014 (ኢዜአ) “የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለአዲስ አበባ ወጣቶች የሰላም፣ የአንድነትና የአብሮነት ማሳያ ነው” ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ፡፡

“አዲስ አበባ የሰላምና የአብሮነት ከተማ” በሚል መሪ ቃል ከተማ አቀፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ተካሂዷል፡፡

በዚሁ ወቅት የተገኙት ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንደገለፁት “ይህ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለአዲስ አበባ ወጣቶች የሰላም፣ የአንድነትና የአብሮነት ማሳያ ነው”፡፡

አዲስ አበባ ምንጊዜም ቢሆን ለስርዓት አልበኝነት እና ለመከፋፈል ምቹ አይደለችም ያሉት ከንቲባ አዳነች ወጣቶችም ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ስታደርጉ ከተማችን ለስርዓት አልበኝነት አትመችም፤ አብሮነቷ ይቀጥላል፤ አንድነቷ ያብባል እያላችሁ መሆን አለበት ብለዋል፡፡

አዲስ አበባችን እንደ ስሟ ውብ፤ በአለም አቀፍ ደረጃ የምታኮራን እንድትሆን እናደርጋታለን ፣ይህንን ማንም ሊያስቆመን አይችልም፤ እኛ ልጆቿ አለን እንተጋለን እንሰራለን ማለታቸውን የከንቲባ ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡

ጤናማና ብቁ አምራች ዜጋ ለመፍጠር ስፖርት ያለውን ጠቀሜታ ከግምት በማስገባት እንዲሁም ስፖርትን በህብረተሰቡ ዘንድ ባህል ለማድረግ የከተማ አስተዳደሩ በሁሉም ክፍለ ከተሞች የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን በየሳምንቱ በቋሚነት እያዘጋጀ መሆኑም ተመላክቷል፡፡