በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ኮንፍረንስ የቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፎች ቀጣይነት ላለው እድገት እንደሚበጁ ተገለጸ

103
ሃዋሳ ግንቦት 10/2010 በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ኮንፍረንስ የቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፎች ቀጣይነት ላለው እድገት እንደሚበጁ ተገለጸ፡፡ በኮንፈረንሱ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ቀጣይነት ላለው እድገት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦና የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን የሚያሳዩ 16 ጥናታዊ ጽሁፎች  ቀርበዋል። ጥናታዊ ጽሁፎቹ ቀጣይነት ላለው እድገት የሚበጁና ለፖሊስ አውጪዎችም ግብዓት እንደሚሆኑ የኮንፍረንሱ ተሳታፊ  ምሁራን ገልጸዋል፡፡ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የአዋዳ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን አቶ ተሻለ ሾዴ  በተለይ ለኢዜአ እንዳሉት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኮሌጁ የሚደረጉ ምርምሮች ቅንጅታዊ አሰራርን ተከትለው ለውጥ እየታየባቸው ነው፡፡ በተለያዩ ዘርፎች የሚደረጉ ምርምሮች ህብረተሰቡን አሳታፊ የሚያደርጉና ጥናቶቹ ለፖሊሲ ግብዓት እንዲውሉ የሚያመቻቹ  ጅምር ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡ "ለመጀመሪያ ጊዜ በኮሌጁ የተዘጋጀው ሃገር አቀፍ የምርምር ኮንፍረንስ ፋይናንስ አስተዳደር ኢንቨስትመንትና የሃገሪቱ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ቀጣይነት ላለው እድገት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦና የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ያሳየ  ነው" ብለዋል፡፡ እንደ ዲኑ ገለጻ የቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፎች የመንግስት ገቢና ወጪ አስተዳደር ላይ የሚታዩ ክፍተቶችና ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች ላይ የበለጠ መስራት እንደሚገባ ያመላከተ ነው፡፡ በኮሌጁ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ተባባሪ ዲን ዶክተር ታምራት ሉደጎ በበኩላቸው ጥናታዊ ጽሁፎቹ ለፖሊሲ አውጪዎች ግብዓት ከመሆን ባለፈ በቴክኖሎጂ የታገዙ ምርምሮችን ወደ ህብረተሰቡ የማሸጋገር ስራ የሚከናወንባቸው እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡ በዚህም በእውቀት ላይ የተደገፈ ግብይት መፍጠርና ሽግግር ላይ ያለውን የሃገሪቱን ኢኮኖሚ ማስቀጠል እንደሚቻልም ጠቁመዋል፡፡ በኮንፍረንሱ ጥናታዊ ጽሁፋቸውን ካቀረቡት መካከል በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር በላይ ጥላሁን  የማክሮ ኢኮኖሚ አለመረጋጋት በሃገሪቱ እድገትና ኢንቨስትመንት ላይ የሚያሳድረውን ተፅእኖ አሳይተዋል፡፡ "ሃገሪቱ ባለሁለት አሃዝ እድገት እያስመዘገበች ቢሆንም የመንግስት ብድር መጨመርና የውጭ ሃገር ምንዛሪ በየዓመቱ መቀያየር በኢንቨስትመንቱ ላይ የሚያሳድሩትን ተጽእኖ  ማክሮ ኢኮኖሚውን በማይጎዳ መልኩ መስተካከተል ይኖርበታል "ብለዋል፡፡ ሌላው ጥናታዊ ጽሁፍ  አቅራቢ የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ኢኮኖሚክስ መምህር መገርሳ ደበላ  ኢንተርፕራይዞች በአዳዲስ የስራ ፈጠራ ተሰማርተው በሃገር ኢኮኖሚ ላይ የሚኖራቸውን ሚና አመላክተዋል፡፡ አዳዲስ የማምረቻና ግብይት ዘዴን መጠቀም፣ በጥናትና ምርምር እንዲሁም በስልጠና ትምህርት የተደገፈና  በድረ ገጽ የታገዙ ኢንተርፕራይዞችን መፍጠር ኢኮኖሚውን ለማሳደግ እንደሚረዳ ገልጸዋል፡፡ "ሃገሪቱ ወደ ኢንዱስትሪ ለምታደርገው ሽግግር ኢንተርፕራይዞች ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው "ያሉት ጥናት አቅራቢው፤ ዘርፉ በጥናትና ምርምር እንዲደገፍ ተቀናጅቶ መስራትና የጋራ መድረኮች መፍጠር እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡ ከግንቦት 8/2010 ጀምሮ ለሁለት ቀናት በተካሄደው የምርምር ኮንፍረንሱ ከሃገሪቱ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ ምሁራን ተሳትፈዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም