በአማራ ክልል በኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ከሶስተኛ ወገን ነጻ የሆነ ከ12 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ ተዘጋጅቷል

121

ደሴ፣ ግንቦት 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል በኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ከሶስተኛ ወገን ነጻ የሆነ ከ12 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ መዘጋጀቱን የክልሉ መሬት ቢሮ አስታወቀ።

በደቡብ ወሎ ዞን በኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ዙሪያ ያሉ ችግሮች ዙሪያ መፍትሔ ማበጀት አላማ ያደረገ ውይይት ዛሬ በደሴ ከተማ ተካሂዷል።

የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሰይፉ ሰይድ በክልሉ መሬት በዘመናዊ የመረጃ ስርዓት ባለመያዙ ለተለያዩ ክርክሮችና ግጭቶች ምክንያት ሆኖ መቆየቱን ገልጸዋል።

በዚህም ምክንያት ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራና የአሰራር ብልሽት መንግስትን ገቢ ከማሳጣት አልፎ ባለሃብቱ የሚፈልገውን መሬት እንዳያገኝና በወቅቱ እንዳያለማ መሰናክል ሆኖ ቆይቷል ብለዋል።

በአማራ ክልል መሬትን በዘመናዊ የመረጃ ስርዓት ለመያዝ እየተከናወኑ ባሉ ስራዎች በክልሉ 75 ወረዳዎች የመሬት ይዞታዎች በመረጃ ቋት ውስጥ እንዲገቡ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

የመረጃ ስርዓት ውስጥ የገቡት አካባቢዎች ላይ ቀደም ሲል ይስተዋሉ የነበሩ ግጭቶችና የፍርድ ቤት ክርክሮች መቀነሳቸውን ነው አቶ ሰይፉ ያስረዱት።

ከሶስተኛ ወገን ነጻ ሆኖ የተዘጋጀው መሬት ግልጽ ጨረታ ወጥቶበት በሂደት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ የተዘጋጀውን መሬት በጨረታ የሚያሸንፉ ባለሃብቶች በውላቸው መሰረት ለታለመለት ዓላማ ማዋል እንደሚኖርባቸው አመልክተዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ፋጡማ ኢማም በበኩላቸው በዞኑ በ2014 ዓ.ም በጀት ዓመት ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡና ከ11 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የስራ ዕድል የሚፈጥሩ 73 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ መውሰዳቸውን ገልጸዋል።

በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት የተሰማሩት ባለሀብት አቶ ነብዩ ነስሩ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢንቨስትመንት ዘርፉ ያሉ የአሰራር መጓተቶችን በክልሉ መሻሻላቸውን ገልጸዋል።

ሌሎች በዘርፉ ያሉ ተዘማች ችግሮችም እንዲፈቱ ጠይቀዋል።

በአማራ ክልል ባለፉት አምስት ዓመታት ከ1 ሺህ 400 ለሚበልጡ ባለሃብቶች ከ190 ሺህ ሄክታር መሬት ተሰጥቶ በተለያዩ ዘርፎች እንዲያለሙ እየተደረገ መሆኑን ከክልሉ የመሬት ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም