ማህበራዊ እሴቶቻችን ለሰላምና ለሀገር ግንባታ እንዲውሉ በማድረግ ረገድ የምሁራን ሚና ከፍተኛ ነው - ሰላም ሚኒስቴር

268

ጎባ፣ ግንቦት 20/2014 (ኢዜአ) የሀገሪቱ ማህበራዊ እሴቶች ለሰላምና ለሀገር ግንባታ እንዲውሉ በማድረግ ረገድ ምሁራን ሚናቸውን እንዲወጡ የሰላም ሚኒስቴር ጠየቀ፡፡

ሚኒስቴሩ ከመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው “የብሔራዊ ምክክሩ እድሎችና ፈተናዎች” በሚል መሪ ሀሳብ ላይ ያተኮረው የሰላም ኮንፈረንስ በባሌ ሮቤ ዛሬ ተካሄዷል፡፡

በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት በሚኒስቴሩ የሰላም ግንባታ ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደኣ እንዳሉት ማህበራዊ ሀብቶቻችን ለሰላምና ለሀገር ግንባታ እንዲውሉ በማድረግ አማራጮችን ማስፋትና ፈተናዎችን በማጥበብ ረገድ የምሁራን ሚና ከፍተኛ ነው፡፡

በተለይ  ሀገር በቀል ማህበራዊ እሴቶቻችንና ባህሎቻችን በልጽገው ለታሰበው አገራዊ ምክክር ውጤታማነት ብሎም ለአገራዊ መግባባቱ እንዲውሉ የምሁራን ድርሻ ከፍተኛ እንደሆነም ነው የገለጹት፡፡

አቶ ታዬ አክለውም ህዝቡን በአንድነትና በመቻቻል ለዘመናት አብሮ ያኖሩ ቱባ ባህላዊ እሴቶቻችን ለሀገር አንድነትና ለሰላም ግንባታ እንዲውሉ ምሁራን በጥናትና ምርምር እንዲደግፉም ጠይቀዋል፡፡

በኮንፈረንሱ ላይ ማህበራዊ ሀብቶቻችን ለሰላም እሴትና ለሀገር ግንባታ መጠናከር 

እንዲሁም ለብሔራዊ ምክክሩ በግብዓትነት መዋል በሚገባቸው ሁኔታዎች ላይም 

ከምሁራን ጋር ምክክር በማድረግ ግብዓት እንደሚወሰድ አቶ ታዬ ጠቁመዋል፡፡

"ኮንፈረንሱ አካታች ብሔራዊ ምክክሩን ከማሳካት አንጻር ለዩኒቨርሲቲው ምሁራን ዕድሎችና ፈተናዎቹን ለመዳሰስ ዕድል የሚፈጥር መድረክ ነው" ያሉት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር አህመድ ከሊል ናቸው፡፡

ዩኒቨርሲቲው የማህበረሰቡ ቱባ ባህሎች በልጽገው ለአገር ሰላምና ሁሉን አቀፍ ብልጽግና እንዲውሉ ለማድረግ ፍላጎትን መሰረት ያደረጉ ምርምሮችና ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎቶችን በምሁራኑ በኩል በማካሄድ ላይ እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡

ከኮንፈረንሱ ተሳታፊ ምሁራን መካከል ረዳት ፕሮፌሰር አሚን መሐመድ ሰላም ወዳድና ለለውጥ የተነሳሳ ማህበረሰብ ለምክክር መድረኩ አጋዥ እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡

እንዲሁም የውጭ ጫናና በህግ ማስከበሩ ላይ አልፎ አልፎ በየቦታው የሚታዩ ክፍተቶች ለአገራዊ ምክክሩ ተግዳሮቶች ሊሆኑ እንደሚችሉና እነዚህን ችግሮች ታሳቢ ያደረጉ ስራዎችን መስራት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡

በሀገሪቱ የተፈጠሩ ችግሮች የማህበራዊ ሀብቶቻችን በአግባቡ በስራ ላይ ያለማዋል ውጤት መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሌላው የመድረኩ ተሳታፊ የነበሩት ረዳት ፕሮፌሰር  አበባ አዱኛ ናቸው፡፡

በተለይ የብሔር ብሔረሰቦች የእርቅ ስርዓቶች በልጽገው ለአገር ልማትም ሆነ ለአገራዊ ምክክሩ በግብዓትነት እንዲውሉ ለማድረግ ከምሁራን የሚጠበቀውን ሚና እንደሚወጡም ተናግረዋል፡፡

በኮንፈረንሱ ላይ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደአንጨምሮ ሌሎች የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ ተማሪዎችና ተጋባዥ እንግዶች ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም