የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከምርታማነቱ ባሻገር ወጪ በመቀነስና የስራ ዕድል በመፍጠር አርሶ አደሮችን ውጤታማ አድርጓል

757

ግንቦት 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከምርታማነቱ ባሻገር በወጪ ቅነሳና የስራ ዕድል በመፍጠር ውጤታማ ያደረጋቸው መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የምንጃር ሸንኮራ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ።

በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ የሸንኮራ ወንዝ ተፋሰስን ተከትለው የሚኖሩ የሶስት ቀበሌ አርሶ አደሮች ከዚህ ቀደም የመስኖ ልማታቸው በሽንኩርት ምርት ላይ ብቻ ያተኮረ እንደነበር አስታውሰው፤ በዘንድሮ የበጋ ወቅት ግን በርካታ አርሶ አደሮች ማሳቸውን በስንዴ ሰብል መሸፈናቸውን ገልጸዋል።

በግብርና ባለሙያዎች አነሳሽነት የጀመሩት የበጋ ስንዴ ልማት በብዙ መልኩ ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በወረዳው የዱበቱ ቀበሌ አርሶ አደሮች እንደሚሉት፤ ለሽንኩርት ምርት ያወጡት ከነበረው ከፍተኛ የጉልበት፣ ገንዘብና ጊዜ አንፃር ስንዴው አዋጭና የተሻለ ምርት የሚገኝበት ሆኖ አግኝተውታል።

የስንዴ የውሃ ፍጆታ ከሽንኩርት አንጻር አነስተኛ እንደሆነ ጠቁመው፤ በመስኖ ያለሙት የበጋ ስንዴ ከመኸር ወቅት ከለማው ስንዴ በተሻለ ምርት እንደሰጠና ለብዙዎች የስራ እድል እንደፈጠረ ተናግረዋል።

በቀጣይ የምርት ዘመን የበጋ ወራት ማሳቸውን በኩታገጠም አርሰው በስንዴና በሌሎች ሰብሎች በስፋት ለመሸፈን እንዳቀዱም ከኢዜአ ጋር ቆይታ የነበራቸው አርሶ አደሮቹ በዩ ገመቹ፣ ግርማ ታዬ፣ አየለ እሸቱና ከበደ ገመቹ ገልጸዋል።

በወረዳው የዱበቱ ቀበሌ ግብርና ጽህፈት ቤት ሃላፊ ተስፋዬ አለሙ፤ በዘንድሮው የበጋ የመስኖ ስንዴ ለማልማት ለአርሶ አደሮች የአስተሳስብ እና ክህሎት ስልጠና ተሰጥቶ ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል።

የግብዓት አቅርቦት በማመቻቸት ለ35 አርሶ አደሮች ማሳቸውን በኩታ ገጠም እርሻ በስንዴ እንዲያለሙ በማድረግ በውሃ አጠቃቅም፣ በገበያ ትስስርና ምርታማነት ውጤታማ ሆኖ ተገኝቷል ብለዋል።

በቀጣይ በስፋት ለማምረት መነሳሳትን መፍጠሩን ገልጸው፤ በዘንድሮው በመስኖ የለማ የበጋ ስንዴ በሄክታር እስከ 60 ኩንታል ለማግኘት እንደታቀደ ተናግረዋል።

የወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት የመስኖ አግሮኖሚ ባለሙያው ሰናይ ነገሠ፤ በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ 1 ሺህ 276 በላይ ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች በመስኖ ለምቷል ብለዋል።

የበጋ መስኖ ስንዴን ለመጀመሪያ ጊዜ በማስጀመር አርሶ አደሩ የምግብ ሰብሎችን በበጋ እንዲያለማ መደረጉን ገልጸዋል። 

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም