በህገ ወጥ መንገድ ቦታ ለመያዝ ሙከራ ሲደረግ በተፈጠረ ግጭት በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ደረሰ

131
አዲስ አበባ ጳጉሜ 4/2010 በፊንፊኔ ዙሪያ በኦሮሚያ ልዩ ዞን በቡራዩ ከተማ አስተዳደር መልካ ገፈርሳ ቀበሌ ልዩ ቦታ ፀበል ማዶ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በህገ ወጥ መንገድ ቦታ ለመያዝ ሙከራ ሲደረግ በተፈጠረ ግጭት በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ደረሰ። የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚገልጹት፤ ከትናንትና በስቲያ በግምት ከቀኑ 9 ሰዓት ከ30 ላይ ራሳቸውን "ቄሮነን" በሚሉ ወጣቶች ጥቃት ደርሶባቸዋል። የመልካ ገፈርሳ ቀበሌ አስተዳደርና የቡራዩ ከተማ ወረዳ 2 ፖሊስ እንደሚናገሩት፤ ቀደም ባሉት ዓመታት አሁን በአካባቢው በሚኖሩ ሰዎች በህገ ወጥ መንገድ የተያዘን ቦታ ዳግም ቄሮዎች በተመሳሳይ መልኩ በህገ ወጥ መንገድ ቦታውን ለመያዝ ሲሞክሩ በተፈጠረ ግጭት ጉዳት ደርሷል። ግጭቱን አስነስተዋል ተብለው የተጠረጡ  አስር ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን የወረዳው ፖሊስ አስታውቋል። የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተሮች ግጭቱ በተከሰተበት ስፍራ በመገኘት ባደረጉት ማጣራት በሸቀጣ ሸቀጥ ሱቆች ላይ ውድመት የደረሰ ሲሆን፤ በጥቂት ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱን አረጋግጠዋል። የአካባቢው ነዋሪ ወጣት አይደር ሙዘይን እንዳለው፤ በንግድ ቤቶች ላይ ውድመት ደርሷል፤ አዛውንቶችም ተደብድበዋል። በአካባቢው ለረጅም ጊዜ እንደኖሩ የሚናገሩት ወይዘሮ ዘምዘም ፈረጃ እንደገለጹት፤ ለዓመታት ከኖሩበት አካባቢ ለቀው እንዲወጡ ጫና የሚያደርጉ ወጣቶች አሉ። አቶ ሙኒር ገብሬ በበኩላቸው፤ የአካባቢው ነዋሪ የሚደርስበትን በደል በማስመልከት በኦሮሚያ ፖሊሲ ኮሚሽን ለቡራዩ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ቢያሳውቁም ምንም ዓይነት ምላሽ እንዳልተሰጣቸው ተናግረዋል። አቶ አክመል ጀመል የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው፤ በአካባቢያቸው በህገ ወጥ መንገድ የታጠረ አጥርን ከነዋሪው ጋር በመተባበር በማፍረስ ጉዳዩን ለፖሊስ እንዳሳወቁ ገልጸዋል። የመልካ ገፈርሳ ቀበሌ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አሚር መሐመድ እንደሚናገሩት፤ በአካባቢው በሁለት ሰዎች መካከል የሚፈጠርን ግጭት የብሔር መልክ እንዲይዝ የሚያደርጉ ሰዎች አሉ። የግጭቱ መንስዔ መሬት በህገ ወጥ መንገድ ለመያዝ በተደረገ ሙከራ እንደሆነም አስረድተዋል። እንደ አቶ አሚር ገለጻ፤ የቀበሌው አስተዳደር ከፖሊስ ጋር በአካባቢው የተፈጠረውን ግጭት ለማስቆም ጥረት በሚያደርግበት ወቅት የአካባቢው ወጣቶች ድንጋይ በመወርወር ጥቃት ለማድረስ ሞክረዋል። ከዚህ በፊት ነዋሪዎቹ በአካባቢው ያለውን ችግር አስመልክተው ለቀበሌው አስተዳደር አሳውቀው እንደማያውቁ የገለጹት አቶ አሚር፤ ለአስተዳደሩ "ከነዋሪዎች ቅሬታ ቀርቦ በዝምታ ያለፈበት ጊዜ የለም" ብለዋል። በኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን የቡራዩ ከተማ ወረዳ 2 ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ሙሉጌታ ለገሰ እንደተናገሩት፤ በአካባቢው ነዋሪዎች በህገ ወጥ መንገድ የተያዘን ቦታ የኦሮሚያ ወጣቶች በተመሳሳይ በህገ ወጥ መንገድ ለመያዝ ሲሞክሩ በተፈጠረ ግጭት በንብረትና በሰው ላይ ጉዳት ደርሷል። ይህን ድርጊት በመቀስቀስ የተጠረጠሩ አስር ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው ነው።     በወቅቱ የተፈጠረውን ችግር ለመቆጣጠር የወረዳው ፖሊስ ከፌዴራልና ከአዲስ አበባ ፖሊስ እንዲሁም ከኦሮሚያ አድማ በታኝ ፖሊስ ጋር በጥምረት መስራቱን ተናግረዋል። በአካባቢው ችግር የሚፈጥሩ ወጣቶች እንዳሉ ነዋሪው ለፖሊስ ጥቆማ እንደሚያደርግ የገለጹት ኮማንደር ሙሉጌታ፤ ፖሊስ ምርመራ በሚያደርግበት ወቅት ጥቆማ የሰጡ ሰዎች "ለምስክርነት ሲጠሩ ፈቃደኛ ስለማይሆኑ ተጠርጣሪዎች ይለቀቃሉ" ብለዋል። በአካባቢው ነዋሪዎች በህገ ወጥ መንገድ የተያዘ መሬት የቀበሌው አስተዳደር ከፖሊስ ጋር በመሆን እርምጃ እንደሚወስድ ኮማንደር ሙሉጌታ ገልጸዋል። ኢዜአ ግጭቱ በተፈጠረበት አካባቢ ተገኝቶ ባደረገው ማጣራት ነዋሪዎቹ ህጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ የሌላቸው መሆኑን አረጋግጧል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም