የፎቶ አውደ ርዕዩ በታሪክ ውጣ ውረድ የነበሩ በርካታ ትምህርቶች የምንወስድበት ነው -ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ

135

ሐረር ፣ ግንቦት 20/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ያዘጋጀው የፎቶ አውደ ርዕይ በታሪክ ውጣ ውረድ የነበሩ በርካታ ትምህርቶች የምንወስድበት ነው ሲሉ የሀረሪ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ተናገሩ።

“ስለ ኢትዮጵያ ” በሚል መሪ ሀሳብ የኢትዮጵያን ዘርፈ ብዙ አሸናፊነት የሚያንፀባርቅ ነው የተባለ የፎቶግራፍ አውደ ርዕይ በሀረር ከተማ ተከፍቷል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ከጅግጅጋ እና ድሬደዋ በመቀጠል ሐረር ከተማ ላይ ዛሬ ያዘጋጀውን የፎቶ አውደ ርዕይ፤ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ የመገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሀመድ እድሪስ እና የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጌትነት ታደሰ ከፍተውታል።

የፎቶ አውደ ርዕዩ ከ1950 ዎቹ ዘመን ጀምሮ ኢትዮጵያን ተስፋ እስከጣለችበት የሪፎርም ለውጥ ማግስት ያለውን ሁለንተናዊ ገፅታ በሚያሳይ መልኩ ለህዝብ እይታ ቀርቧል።

በወቅቱም የሀረሪ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ እንደተናገሩት በአውደ ርዕዩ የቀረቡት ፎቶዎች የታሪክ ውጣ ውረዶች በርካታ ትምህርቶች የምንወስድባቸው ናቸው ።

ኤግዚቢሽኑ ከዘውዳዊው አገዛዝ ጀምሮ የህዝቡን ጥያቄ ምን እንደነበር እና ህዝብ ከመንግስት ጋር ከሰራ ማንኛውንም ፈተና መሻገር እንደሚቻል ያሳየመሆኑን ገልጸዋል ፡፡

"የዲሞክራሲያዊ ጥያቄ መሰረታዊ ነው ጥያቄው ካልተፈታ ሌሎች ችግሮች ሊፈቱ አይችሉም" ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ የዛሬ ጥንካሬዎችን ማስቀጠል ድክመቶችን መቅረፍ የነገ ስጋትን በማስወገድ ተስፋ እንዲለመልም እና እንዲበለፅግ ማድረግ ያስፈልጋል " ነው ያሉት ፡፡

ርእሰ መስተዳድሩ "ልዩነት ጌጣችን ነው የምንከፋፈልበት የምንገፋፋበት ሳይሆን በአካታችንት የምንሰራበት መሆን አለበት " ብለዋል ፡፡

በመሆኑም ፅንፈኝነት እና መገፋፋትን በመታገል ነባር የወንድማማችነት እሴቶችን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል ፡፡

"አገራችን በአሁኑ ጊዜ የሁሉንም ርብርብ ትጠይቃለች ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ ሁሉም በተለይ ሚዲያው የበኩሉን ሚና በመወጣት አሻራውን ሊያሳርፍ ይገባል ብለዋል ፡፡

የኢትዮጵያ ብዙሃን መገኛኛ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሀመድ ኢድሪስ ሚዲያዎች ታሪክን በመሰነድ፣ አብሮነትን በማጎልበት፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን በማጠናከር እና ኢትዮጵያን ለማሻገር እና ከፍ ለማድረግ ድልድይ መሆን አለባቸው ሲሉ ተናግረዋል ፡፡

ከዚህ በተፃራሪ የሚንቀሳቀሱ ሚዲያዎችን ህዝቡ በቃቹ ሊላቸው እንደሚገባ ጠቁመው መንግስት በጀመረው የህግ ማስከበር እርምጃ የህግ የበላይነት የማስከበሩ ስራ ይሰራል ብለዋል ፡፡

"ታሪክን መካድ አያስፈልግም ይልቅ ታሪክን በሚጠቅመን መንገድ መረዳት ያስፈልጋል " ሲሉም ተናግረዋል ፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጌትነት ታደሰ ድርጅቱ ለ 82 አመታት የህዝብ የህትመት ሚዲያ በመሆን ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል ፡፡

ድርጅቱ በሚሰራቸው ስራዎች ለቋንቋ ለስነፅሁፍ ለጥናትና ምርምር ለጋዜጠኝነት ሞያ እድገት ከፍተኛ አስተዋፆ ሲያደርግ የቆየ ሚዲያ መሆኑንም ገልፀዋል ፡፡

አውደ ርእዩን በ 11 ከተሞች ለማከናወን እቅድ መያዙንም አክለዋል።

ባለፉት ጊዜያት ያጋጠሙ ችግሮች ላይ ብሎም በኢትዮጵያዊነት የጋራ እሴቶች ላይ ውይይቶች እንደሚደረጉም ተናግረዋል፡፡

ለአራት ቀናት በሚቆየው በዚህ የፎቶግራፍ አውደርእይ ላይ የምስራቅ ተጎራባች ክልሎች አመራሮች፣ ባለሀብቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች የክልሉ ማህበረሰብ ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም