አመራሩ በኢትዮጵያዊነት ተሳስሮ ሀገርንና ህዝብን ለማሻገር መስራት እንዳለበት ተጠቆመ

96

ሚዛን አማን፣ ግንቦት 20/2014( ኢዜአ) በኢትዮጵያዊነት የአብሮነት ቀለበት ተሳስሮ ሀገርንና ህዝብን ለማሻገር መስራት ከአመራሩ እንደሚጠበቅ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት አስታወቀ።

በክልሉ ለብልጽግና ፓርቲ አመራሮች "አዲስ ፖለቲካዊ እይታ ለአዲስ ሀገራዊ እመርታ" በሚል መርህ በሚዛን አማን ማዕከል ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ትናንት ማምሻውን ተጠናቋል።

በማጠቃለያ መድረኩ ላይ የተገኙት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው እንዳሉት "የመደመር ዘመን አመራር ራሱን በእውቀትና በክህሎት እያሳደገ ለውጡን እውን ለማድረግ የሚሰራ ነው"።

በመሆኑም በኢትዮጵያዊነት የአብሮነት ቀለበት ተሳስሮ ሀገርና ህዝብን የሚያሳድግና የሚያሻግር ተግባራዊ ሥራ ማሳየት እንደሚገባው ነው ያስገነዘቡት።

"ቃልን በተግባር ማሳየት የብልጽግና መርህ በመሆኑ በየአካባቢው ለህዝቡ ለመስራት ቃል የተገቡ ጉዳዮች እንዲፈጸሙ በአገልጋይነት መንፈስ መትጋት ይኖርብናል" ነው ያሉት።

በመደመር እሳቤ አንዱ ከሌላው በመማማር ጉድለቶችን በጋራ ሞልቶ ለውጤት መስራት ሊለመድ የሚገባው ጉዳይ መሆኑንም አቶ ማስረሻ አመላክተዋል።

"እንደ ብልጽግና አመራር ሚዛናዊነትን ጠብቆ መንቀሳቀስና ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል በእኩል ዓይን ማሳተፍና ማስተናገድ ይገባል" ሲሉም አሳስበዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጽህፈት ቤት የፖለቲካና ርዕዮተ ዓለም ዘርፍ ኃላፊ አቶ ተዘራ ወልደማርያም በበኩላቸው፣ አመራሩ በሚፈለገው ልክ "ህዝብና ሀገርን እንዲያገለግል የተግባርና የአስተሳሰብ አንድነቱ መጎልበት አለበት" ብለዋል።

ብሔራዊ ጥቅምና ዘላቂ ሰላምን የሚያረጋግጡ ጉዳዮች ላይ ቅድሚያ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት።

አቶ ተዘራ እንዳሉት የፓርቲውን ፕሮግራምና የመደመር እሳቤ መሠረታዊ ጉዳዮችን ቀጣይነት ባለው መልኩ በመተግበር ህብረተሰቡን ለማገልገል የሚችል ብቁ አመራር ለመፍጠር እየተሰራ ነው።

ላለፉት አምስት ቀናት የተሰጠውን የአመራር አቅም ማጎልበቻ ስልጠናንም ለእዚህ በማሳያነት ጠቅሰዋል።

በሚዛን ማዕከል ስልጠናውን ከወሰዱ አመራሮች መካከል አቶ ዮናስ ኬና ስልጠናው በርካታ የአስተሳሰብ ለውጦችን እንዲያመጡ ያደረጋቸው መሆኑን ገልጸዋል።

መጀመሪያ የነበራቸውን የመፈጸም አቅምና የህዝብ አገልጋይነት ተነሳሽነታቸውን ከፍ እንዳደረገውም አክለዋል።

"ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ በመገንዘብ በመደመር እሳቤ ሀገራዊ ለውጡን ቀጣይ ለማድረግ ከህብረተሰቡ ጋር ጠንክረን እንሰራለን" ብለዋል።

በሚዛን አማን ከተማ በተሰጠው የአመራር አቅም ማጎልበቻ ስልጠና ከቤንች ሸኮ፣ ከሸካ እና ምዕራብ ኦሞ ዞን የተውጣጡ 220 አመራሮች መሳተፋቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም