የለገዳዲ ክፍል ሁለት ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ ፕሮጀክት በተያዘው በጀት ዓመት ማጠናቀቂያ ላይ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል

94

ግንቦት 20/2014 (ኢዜአ) የለገዳዲ ክፍል ሁለት ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ ፕሮጀክት በተያዘው በጀት ዓመት ማጠናቀቂያ ላይ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች እና ስፖርት ኮሚሽን ከአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ጋር በመተባበር የመዲናዋን የውሃ አቅርቦት አስመልክቶ የተለያዩ የውሃ ማጣሪያ ጣቢያዎችን ለወጣቶች አስጎብኝተዋል።

ወጣቶቹ በጉብኝታቸው የቃሊቲ ፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ፣ የአቃቂ የከርሰ ምድር ውሃ ጣቢያ እንዲሁም የለገዳዲ ቁጥር አንድ እና ሁለት የማስፋፊያ ፕሮጀክቶችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

የጉብኝቱ ዓላማ ወጣቶች ለውሃ አገልግሎት የሚውሉ መሰረተ-ልማቶችን አውቀው እንዲጠብቋቸው ማስቻል እና በመሰረተ-ልማቶች ላይ የሚፈጸመውን ስርቆት እንዲከላከሉ ግንዛቤ ማስጨበጥ መሆኑ ተመላክቷል።

እንዲሁም ከውሃ አጠቃቀም አንጻር ያለውን ብክነት ለመከላከል በሕብረተሰቡ ውስጥ የግንዛቤ ማስጨበጫዎች እንዲሰጡ ለማድረግ መሆኑም ተገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አብርሃም ታደሰ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በተለያዩ ጊዜያት በመዲናዋ የሚሰሩ የልማት ሥራዎችን ለወጣቶች የማስተዋወቅና እንዲጎበኙ መደረጉን ጠቁመዋል።

ያሁኑ ጉብኝትም የመጠጥ ውሃን ለማምረት ያለውን ልፋት በማሳየት በውሃ ብክነት ላይ ያለውን ችግር ተባብረው እንዲሰሩ ማስቻል መሆኑን ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሰርካለም ጌታቸው በበኩላቸው፤ በጉብኝቱ ወቅት የመጠጥ ውሃን ለማምረት ከማጣራት ጀምሮ ያሉ ሥራዎች በሚመለከት ለወጣቶቹ ገለጻ እንደተደረገላቸው ተናግረዋል፡፡

በዚህም ወጣቶቹ በቀጣይ ወደ አካባቢያቸው ሲመለሱ የውሃ ብክነትን ለመከላከል የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ይጠበቃል ብለዋል።

ከጎበኟቸው ፕሮጀክቶች መካከል የለገዳዲ ክፍል ሁለት ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ ፕሮጀክት በተያዘው በጀት ዓመት መጨረሻ ለአገልግሎት እንደሚበቃም ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ በ4 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር የተገነባ መሆኑን ገልጸው፤ ወጪው ሙሉ በሙሉ በመንግሥት መሸፈኑንም ጠቁመዋል።

ፕሮጀክቱ ተጠናቆ ወደሥራ ሲገባ በቀን 86 ሺህ ሜትር ኪዩብ መስጠት ይችላል ያሉት ወይዘሮ ሰርካለም፤ በዚህም የካ ክፍለ ከተማን ሙሉ በሙሉ እንዲሁም ጉለሌን በከፊል ውሃ የማዳረስ አቅም እንዳለው ገልጸዋል።

የጉብኝቱ ተሳታፊ ወጣቶች በጉብኝታቸው በርካታ እውቀት ማግኘታቸውን ገልጸው፤ ሁሉም ዜጋ የውሃ ሃብትን ከብክነት በመከላከል ረገድ የበኩሉን ሚና መወጣት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም