በዞኑ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የፍራፍሬ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት ተደርጓል

188

መቱ ግንቦት 20/2014 (ኢዜአ) በመጪው ክረምት ከሁለት ሚሊዮን በላይ የፍራፍሬ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የኢሉባቦር ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት ገለጸ፡፡

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የደን ሽፋንን ለማሳደግ ከሚተከሉ የዛፍ ችግኞች ባሻገር ለምግብነትና ለሌላ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ የሚውሉ የተለያዩ የፍራፍሬ ችግኞችን በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች ለመትከል እየተሰራ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡

የኢሉባቦር ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ቻላቸው አዱኛ እንደገለጹት በመጪው ክረምት ከሁለት ሚሊዮን በላይ የተለያዩ የፍራፍሬ ዓይነት ችግኞች ይተከላሉ።

ለዚህም ከ10 ሺህ በላይ ሔክታር መሬት መዘጋጀቱን የገለጹት ምክትል ሃላፊው፤ ሙዝ፣ ፓፓያ፣ ማንጎና የአቦካዶ ችግኞች ደግሞ ከሚተከሉት የፍራፍሬ ዓይነቶች ዋነኞቹ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ለፍራፍሬ መትከያ ከተዘጋጀው 10 ሺህ ሔክታሩ ውስጥ ወደ 200 የሚሆኑት የመትከያ ቦታዎች በኩታ ገጠም የሚተከልባቸው መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

በዞኑ የመቱ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸው ረጋሳ በወረዳው ለፍራፍሬ ተክሎች ትኩረት በመስጠት ባለፈው ዓመት አቦካዶን በኩታ ገጠም መትከል መጀመራቸውን አስታውሰዋል።

በዚህ ዓመት ሁለት መቶ ሺህ የሚደርሱ የሙዝና የአቡካዶ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት ማጠናቀቃቸውንም አክለዋል።

አቶ መዝገቡ ባቡ ደግሞ በዞኑ የመቱ ወረዳ ነዋሪ ሲሆኑ እንደ ሙዝና አቦካዶ ያሉ ተክሎች ለምግብነት ከሚሰጡት ጥቅም በተጨማሪ በከፍተኛ ሁኔታ በገበያ ውስጥ ተፈላጊ ስለሆኑ ትልቅ የገቢ ማሳደጊያ እንደሚሆናቸው ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜም ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር የፍራፍሬ ችግኞችን በጋራ በኩታ ገጠም ለመትከል ዝግጅቶችን እያጠናቀቁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በዞኑ የበቾ ወረዳ ነዋሪ አቶ አበራ ገለታ በበኩላቸው ከዚህ በፊት ለሰብል እህሎች ብቻ ትኩረት ሰጥተው ሲሰሩ እንደነበር አንስተው፤ በአሁኑ ወቅት በገበያው ላይ ያለው የፍራፍሬ ተፈላጊነትና ዋጋው ጭምር የፍራፍሬ ችግኞችን እንዲተክሉ እንዳነሳሳቸው ገልጸዋል፡፡

በግብርና ባለሙያዎች እየተሰጣቸው ባለው የሙያ ድጋፍ ታግዘው የቦታ ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውንም አክለዋል።

ምርታማ ናቸው የተባሉ የአቦካዶ፣ የፓፓያና የሙዝ ዝሪያዎች በግብርና ጽሕፈት ቤት በኩል እንደሚቀርብላቸውና ተመዝግበው በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውንም እንዲሁ፡፡

የመቱ ወረዳ ነዋሪ አቶ ተስፋዬ ዴሬሳም ከዚህ በፊት የተወሰኑ የአቦካዶ ችግኞችን በጓሯቸው ተክለው ከጠበቁት በላይ ጥቅም እንዳገኙበት አንስተውልናል።

አቶ ተስፋዬ በዚሁ ጊዜ እንደነገሩን ባለፈው ዓመት ከአቦካዶ ምርቱ ሃያ ሺህ ብር ያህል ገቢ እንዳገኙና ይህም ለፍራፍሬ እርሻው ትኩረት እንዲሰጡ እንዳነሳሳቸው ተናግረዋል።

በዚህ ወቅትም ለአቦካዶና ሙዝ ተከላ የቦታ ዝግጅት በማጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን ነግረውናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም