ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለአፍሪካ የሚያደርገውን የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያጠናክር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጥሪ አቀረቡ

107


ግንቦት 19 ቀን 2014 (ኢዜአ) ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በሰብዓዊ ድጋፍ ለአፍሪካ የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ እንዲያጠናክሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጥሪ አቀረቡ።


ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ልዑካን ቡድናቸው በማላቦ እየተካሄደ በሚገኘው በ15ኛው የአፍሪካ ህብረት የሰብአዊ እርዳታ እና ቃል ኪዳን ጉባኤ ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ።


በጉባኤው ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እንደገለፁት የአፍሪካ ቀንድ በዓለም በአየር ንብረት ለውጥ እና በድርቅ ሳቢያ የከፋ ሰብዓዊ ቀውስ ከተከሰተበት ቀጠናዎች አንዱ ነው።


ይህንንም የተፈጥሮ አደጋ ጉዳት ለመቀነስ ከአጋር አካላት ጋር በመሆን በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ናቸው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።


ከዚህ ቀደም በቀጠናው የተከሰተው ተከታታይ ድርቅ እንደሚያሳየው ጠንካራ የአደጋ መከላከል እርምጃ ወሳኝ እንደሆነም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለፁት።


በኢትዮጵያ ባለው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር አገሪቱ በዓመት በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል በሚቀጥሉት ጊዜያት በአየር ንብረት ለውጥ ሊመጣ የሚችለውን ፈተናዎች ለመቋቋም የጀመረችውን ስራ አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።


በዓለም የከፋ የኢኮኖሚ የዋጋ ግሽበት እየታየ ቢሆንም አገሪቱ ለዓለም አቀፍ ስደተኞች እና ከቀያቸው ለተፈናቀሉ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ መስጠቷን አጠናክራ ቀጥላለች ብለዋል።


ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በአህጉሪቱ በተለይ በአፍሪካ ቀንድ ያለውን የሰብዓዊ እርዳታ ለማሳለጥ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩም ጥሪ ማቅረባቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።


ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም