ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ከጃፓን መንግሥት ከፍተኛ የክብር ሽልማት ተበረከተላቸው

150

ግንቦት 19/2014/ኢዜአ/ የአርማወር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ከጃፓን መንግስት "ኦርደር ኦፍ ዘ ራይዚንግ ሰን ጎልድ ኤንድ ሲልቨር ስታር" የተሰኘ ከፍተኛ የክብር ሽልማት ተበርከተላቸው።

ሽልማቱን በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢኮ ታካኮ በአገሪቱ ንጉሥ ስም አበርክተውላቸዋል።

"ኦርደር ኦፍ ዘ ራይዚንግ ሰን ጎልድ ኤንድ ሲልቨር ስታር" ሽልማት እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር  1875  የተጀመረ የጃፓን መንግሥት የክብር ሽልማት ሲሆን፤ በጃፓንና ወዳጅ ሀገራት ግንኑነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላደረጉ አገራት የሚሰጥ ነው።

የዛሬው ተሸላሚ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ የኢትዮጵያና ጃፓን ግንኙነት የበለጠ እንዲጠናከር የካይዘን አሰራርን በማስተዋወቅ ለነበራቸው ሚና፣ በአፍሪካ ልማት ላይ አተኩሮ በሚካሄደው የቶኪዮ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ (ቲካድ) ላላቸው የነቃ ተሳትፎ እንዲሁም በጃፓን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ያለው የምሳ ምገባ ስርዓት በኢትዮጵያ እንዲጀመር ላሳዩት ፍላጎት የክብር ሽልማቱ እንደተበረከተላቸው አምባሳደር ኢኮ ታካኮ ተናግረዋል።

ፕሮፌሰር አፈወርቅ በሁለቱ አገራት ዩኒቨርሲቲዎች መካከል የምርምርና ሌሎች ትምህርታዊ ግንኙነቶች እንዲጠናከሩ በጎ ሚና መጫወታቸውንም አምባሳደሯ ጠቅሰዋል።

በዚህም የጎንደር ዩኒቨርሲቲና ቶኩሺማ ዩኒቨርሲቲዎች በጋራ እንዲሠሩ ያደረጉትን ስምምነት ለአብነት አንስተዋል፡፡

ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ለተበረከተላቸው ሽልማት ምስጋና አቅርበው፤ በቀጣይ ኢትዮጵያና ጃፓን ያላቸው ግንኙነት እንዲጠናከር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ተናግረዋል፡፡

ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ከዚህ ቀደም በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታነት፣ በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታነት ያገለገሉ ሲሆን አሁን የአርማወር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ናቸው።

በሽልማት ስነ-ስርዓቱ ላይ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣  አምባሳደሮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም