የባንክ አገልግሎትን ቀስ በቀስ ለዓለም አቀፍ ውድድር ክፍት በማድረግ ባንኮች አቅማቸውን እያጎለበቱ እንዲሄዱ መስራት ይገባል

86

ግንቦት 19/2014/ኢዜአ/  የአገር ውስጥ የባንክ አገልግሎትን ቀስ በቀስ ለዓለም አቀፍ ውድድር ክፍት በማድረግ ባንኮች አቅማቸውን እያጎለበቱ እንዲሄዱ መስራት እንደሚገባ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ ተናገሩ።

መንግሥት የአገር ውስጥ ባንኮች ከአቅም በላይ በሆነ ውድድር ከገበያ ውጭ እንዳይሆኑ ለማድረግ  የባንኩን ዘርፍ ለዓለም ገበያ ዝግ አድርጎ መቆየቱ ይታወሳል።

አቶ አቤ ሳኖ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ የባንኩን ዘርፍ ለዓለም ገበያ ዝግ በማድረግ የአገር ውስጥ ባንኮችን አቅም መገንባት እንደማይቻል ተናግረዋል።

የባንክ አገልግሎቱን እንደተዘጋ ማቆየት የአገር ውስጥ ባንኮችን እድገት እንደሚያቀጭጨውም ነው የገለጹት።

በተቃራኒው የባንክ አገልግሎቱን ድንገት ለዓለም ገበያ ወለል አድርጎ መክፈትም የአገር ውስጥ ባንኮች እንዲዋጡ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።

በመሆኑም የባንክ አገልግሎቱን ቀስ በቀስ ለዓለም አቀፍ ውድድር ክፍት በማድረግ የአገር ውስጥ ባንኮች የውድድር አቅማቸውን እያጎለበቱ እንዲሄዱ መሥራት እንደሚገባ ነው የገለጹት።

የባንኮች አቅም የሚገነባው ገበያውን በመዝጋት ሳይሆን በልካቸው የሚወዳደሩበትን አሰራር በመዘርጋት መሆኑንም ጠቁመዋል።

ውድድር ዓለም አቀፍ ልምዶችን ለመቅሰም ዕድል እንደሚፈጥር ጠቅሰው፤ በውድድሩ የአገር ውስጥ ባንኮች እንዳይጎዱ በበቂ ጥናት ላይ የተመሰረተ ፖሊሲ ያስፈልጋል ብለዋል።

በተወሰነ የአክሲዮን ድርሻ የውጭ ባንኮች እንዲገቡ በማድረግ በሂደት የአክሲዮን መጠናቸውን እያሳደጉ የሚሄዱበትን አሰራር መዘርጋት እንደሚገባ አመላክተዋል።

ይህን ማድረግ የአገር ውስጥ ባንኮችን ባጠረ ጊዜ ወደተሻለ ብርታት ሊያመጣቸው እንደሚችልም ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የባንክ ዘርፉ ለውጭ ገበያ ዝግ ሆኖ መቆየቱ የራሱ ጠቀሜታ እንደነበረው ጠቅሰው፤ አገር ተጨማሪ ሀብትና የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ስላለባት የፖሊሲ ማሻሻያ እንደሚደረግ መናገራቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም