የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኢትዮጵያ ለጅቡቲና ኤርትራ ስምምነት ያደረገችውን አስተዋጽኦ አደነቀ

107
አዲስ አበባ ጳጉሜ 4/2010 ኢትዮጵያ ለጅቡቲና ለኤርትራ ስምምነት ላደረገችው አስተዋጽኦ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ አድናቆታቸውን ገለጹ። ዋና ጸሃፊው ኢትዮጵያ፤ ኤርትራ፣ ሶማሊያና ጅቡቲ በቀጠናው ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን እንዲቻል የደረሱበት የጋራ ስምምነት ለምስራቅ አፍሪካና ለሌሎች አገሮች ምሳሌ የሚሆን ነው ብለዋል፡፡ ጉቴሬዝ አገራቱ አሁን እያስገኙ ያሉት በጎ ጅምሮች እንዲጠናከሩ ለማድረግ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከጎናቸው እንደሚሆን መናገራቸውንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል። በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከሶማሊያው ፕሬዝዳንት ጋር ወደ ኤርትራ በሄዱበት ወቅት በጅቡቲና በኤርትራ መካከል የተፈጠሩት ችግሮች መፈታት እንዳለባቸው ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር የጋራ መግባባት ላይ መድረሳቸው አይዘነጋም፡፡ ይህንን ተከትሎ የኢትዮጵያ፣ የኤርትራና የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በጅቡቲ በተገኙበት ወቅት ፕሬዝዳንት ኦማር ጊሌ የኢትዮጵያ መንግስት ከኤርትራ ጋር ያለባቸውን ችግሮች እንዲፈቱ እያደረገ ላለው አስተዋጽኦ ማመስገናቸው ይታወሳል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም