ህግ የማስከበር ዘመቻው የሕዝቡን ሰላም በማረጋገጥ የልማት ስራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ያለመ ነው

152

ደብረ ማርቆስ ግንቦት 19/2014/ ኢዜአ/ በምስራቅ ጎጃም ዞን እየተካሄደ ያለው ህግ የማስከበር ዘመቻ የህዝቡን ሰላምና ደህንነት በማረጋገጥ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ዓላማ ያደረገ መሆኑን የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ ገለጹ።

ምክትል አስተዳዳሪው አቶ መንበሩ ዘውዴ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የማህብረሰቡን ሰላም በመንጠቅ  እኩይ ዓላማቸውን በሀይል ለማስፈጸም የሚንቀሳቀሱ ህገ-ወጦችን ከዚህ በላይ አንታገስም ነው ያሉት።

በየአካባቢው በቡድን በመደራጀትና በተናጠል የሚንቀሳቀሱ ህገ ወጦች ህብረተሰቡን ሰላም በመንሳት፣ ልማትን የማደናቀፍና በመንግሥት ላይ ጫና የማሳደር ሙከራዎች ሲያደርጉ እንደነበር ገልፀዋል።

ስለሆነም መንግሥት የህብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅና መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን ለማድረግ ህገወጦችን በቁጥጥር ስር በማዋል ህግ የማስከበር እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ተናግረዋል።

በተወሰደው እርምጃም 527 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በህግ እየታየ መሆኑን ምክትል አስተዳዳሪው አብራርተዋል።

ከተጠርጣሪዎቹ መካከል በፋኖ ስም በመንቀሳቀስ በህዝብ ላይ ህገወጥ ተኩስ፣ ዝርፊያና የተለያዩ ህገ-ወጥ ተግባራት ሲፈጽሙ የነበሩና በጥናት የተለዩ ይገኙባቸዋል።

ከዚህም ባሻገር የአሸባሪውን ህወሓት ተልዕኮ ይዘው ሲንቀሳቀሱና በሀሰተኛ ወሬ ህብረተሰቡን ለግጭት ለመዳረግ ሲሰሩ የነበሩም እንደሚገኙባቸው አስታውቀዋል።

በህግ ማስከበር እርምጃም የጥይት ተኩስን ጨምሮ ህብረተሰቡን እረፍት የነሱ፣ ስርቆትና ሌሎች ወንጀሎች ከመቀነሳቸውም በላይ በአካባቢው የተሻለ ሰላም እንዲኖር አድርጓል ብለዋል።

በተለይ ጥይት በመተኮስ ህጻናትና እናቶችን የማሸበር ድርጊት ሙሉ በሙሉ ማስቆም መቻሉን ገልጸዋል።

ለህግ ማስከበር እርምጃው ህብረተሰቡ ተፈላጊዎችን አጋልጦ በመስጠትና በመጠቆም ከፍተኛ ድርሻ ማበርከቱንም ተናግረዋል።

ምክትል አስተዳዳሪው በመግለጫቸው እንዳስታወቁት በዞኑ ህብረተሰቡን ባሳተፈ አግባብ የተጀመረው ህግ የማስከበር ዘመቻ ተጠናክሮ ይቀጥላል።

ህብረተሰቡም ከዚህ በተቃራኒ ለሚናፈሱ መሰረተ-ቢስ ወሬዎች ጀሮ ባለመስጠት ያለውን ነባራዊ ሀቅ በመገንዘብ ከፀጥታ አካሉ ጎን በመሆን ህገወጦችን በመጠቆም የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም