የግዥ ሕጉን በመተላለፍ በበጀት መዝጊያ ወቅት ግዥ በሚፈጽሙ ተቋማት ላይ ሕጋዊ እርምጃ ይወሰዳል

123

ግንቦት 19/2014(ኢዜአ)  የግዥ ሕጉን በመተላለፍ በበጀት መዝጊያ ወቅት ግዥ በሚፈጽሙ የመንግሥት ተቋማት ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ የመንግስት የግዥና ንብረት ባለሥልጣን አስጠነቀቀ፡፡

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሃጂ ኢብሳ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የመንግሥት ተቋማት በዓመት ሁለት ጊዜ ግዥ መፈጸም እንደሚችሉ የግዥ ሕጉ ይደነግጋል።

ይህም በበጀት ዓመቱ አንደኛው ሩብ ዓመት ከሐምሌ እስከ መስከረም እንዲሁም በሦስተኛው ሩብ ዓመት ከታህሳስ እስከ የካቲት መሆኑን አብራርተዋል።

በመሆኑም በጀት መዝጊያን ጠብቆ  የሚፈጸሙ አላስፈላጊ ግዢዎች ተቀባይነት የሌላቸው ከመሆናቸው ባሻገር ለሌብነት በር የሚከፍቱ ናቸው ብለዋል።

ባለሥልጣኑ ከሚያዚያ 20 ቀን 2014 ዓ.ም በኋላ ተቋማት ምንም አይነት ግዥ እንዳይፈጽሙ የሚያስገነዝብ ደብዳቤ ለሁሉም ተቋማት መላኩን አንስተዋል።

በመሆኑም የግዥ ህጉን ተላልፈው በጀት መዝጊያ ወቅት ግዥ የሚፈጽሙ ተቋማት ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ አስጠንቅቀዋል፡፡

ተቋማት ይህን ተገንዝበው ካላስፈላጊ ግዢዎች ሊታቀቡ እንደሚገባም ነው ዋና ዳይሬክተሩ ያሳሰቡት።

በልዩ ሁኔታ የሚታዩ የመድኃኒት፣የምግብና መሰል ግብዓቶች ግዥ ሲያስፈልግ ሕጋዊ መንገዱን በጠበቀ መልኩ ፈቃድ በመውሰድ ግዥ እንደሚፈጸም ተናግረዋል፡፡

የተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ለሕጉ ተፈጻሚነት በባለቤትነት መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበው፤ ከዚህ አኳያ ባለሥልጣኑ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቋሚ ኮሚቴ አባላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ አክለዋል።

በተጨማሪም ተጠሪ ተቋማትና መገናኛ ብዙኃን አስፈላጊውን ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ረገድ የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

የማዕቀፍ ግዢ ሂደትን ተከትሎ የሚፈጠር የተንዛዛ አሰራርን ለማስቀረትም የኤሌክትሮኒክስ ግዢ መፈጸሚያ ሥርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝም አብራርተዋል፡፡

ቴክኖሎጂው ዓለም አቀፍ ግዢዎችን ጭምር በቀላሉ ለመፈጸም የሚያግዝ መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡

የሚገዙ የእቃ አይነቶችና ብዛት፣ የጨረታ መወዳደሪያ ማስታወቂያና ሕግ እንዲሁም ከጨረታ አሸናፊ ተቋማት ጋር የሚደረግ የውል ስምምነት ፊርማን ጨምሮ በዚሁ የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት የሚሰጥ ይሆናል ነው ያሉት፡፡

ቴክኖሎጂው ሥራን ከማቃለሉ ባሻገር ግዥን ምክንያት በማድረግ የሚፈጸም ሙስናና ሌብነትን ለመቅረፍ እንደሚያግዝም ነው ጨምረው የገለጹት፡፡

ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ቴክኖሎጂውን በባለቤትነት የሚመራው ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት የራሱ የሆነ ሴክተር እየተቋቋመለት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ሰባት ተቋማትን ከቴክኖሎጂው ጋር በማስተሳሰር ስኬታማነቱን ማረጋገጥ መቻሉን ገልጸው፤ በአሁኑ ወቅት ቴክኖሎጂውን በ63 ተቋማት ተግባራዊ ለማድረግ የማሰልጠንና የማስተሳሰር ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡

ቴክኖሎጂው ከቀጣዩ በጀት ዓመት መጀመሪያ ሐምሌ ወር ጀምሮ ሙሉ ለሙሉ ወደ ሥራ እንደሚገባም ዋና ዳይሬክተሩ አረጋግጠዋል።  

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከዚህ ቀደም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር በልዩ ሁኔታ ከሚፈቀዱ ግዥዎች በስተቀር ተቋማት ከግንቦት ወር በኋላ ግዥ እንዳይፈጽሙ ማሳሰባቸው ይታወሳል፡፡   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም