ክልሉን የግጭት ማዕከል ለማድረግ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል- ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳው

176

ግንቦት 19 ቀን 2014 (ኢዜአ) በብሔር ስም እየነገዱ ክልሉን የግጭት ማዕከል ለማድረግ የሚንቀሳቀሱ ፀረ-ሠላም ኃይሎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳው አስታወቁ።

የደቡብ ክልል የፀጥታ ምክር ቤት በወቅታዊ ክልላዊ የፀጥታ ሁኔታ እንዲሁም የክልሉን ሠላምና ደህንነት በማስመልከት የተከናወኑ ተግባራትና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ ውይይት መድረክ በወላይታ ሶደ ከተማ እየተካሄደ ነው።


በዚህ ወቅት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው እንዳሉት በሀገራዊ ለውጡ ማግስት ያለፈው ሥርዐት ብልሹና ከፋፋይ አስተሳሰብ መሠረት ያደረጉ ግጭቶች መከሰታቸውን አስታውሰው በዚህም በርካታ ጥፋት ደርሷል ብለዋል።


ይህንን ጥፋት ለማስቆም በተለይ በክልሉ ክህዝቦች ጋር በቅርበት በተከናወኑ ስራዎች ባለፉት ሁለት አመታት በክልሉ አንፃራዊ ሠላም ማስፈን መቻሉንና በተገኘው ሠላም ወደ ልማት በመዞር ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየቱን ጠቅሰዋል።


ሆኖም በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች ላይ የተራዘሙ ግጭቶች እየተስተዋሉ ነው ያሉት አቶ ርስቱ በቅርቡ በደራሼ ልዩ ወረዳ አካባቢ የተከሰተው ግጭት የፀጥታ አካላትንም ጭምር ለአሰቃቂ መስዋዕትነት የዳረገ መሆኑን አውስተዋል።


በተለይም በደራሼ ፣ ኮንሶ ፣ ኧሌ እና አካባቢው ላይ ግጭቶችን ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ አካላት ቀጠናውን እያወኩ ፣ የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እየገቱ እንደሚገኙ ገልጸው እነዚህ አካላት በብሔር ስም የሚነግዱና ክልሉን የግጭት ማዕከል የማድረግ ዓላማ ያነገቡ መሆናቸውን አስታውቀዋል።


የክልሉ መንግስት ባለፈው አንድ ወር እነዚህን አካባቢዎች ከማረጋጋት ባለፈ ሕግን የማስከበር ሥራዎችን ሲሰራ መቆየቱን ጠቁመው አሁንም በፀረ ህዝብ በሆኑት ኃይሎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በደራሼ አካባቢ ተፈጥሮ በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት በጥፋተኝነት የተጠረጠሩ ከ450 በላይ ግለሰቦችና 17 አመራሮችና የፀጥታ አካላት በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን እንዲሁም በደቡብ ኦሞ ዞን አካባቢ ደግሞ 650 የሚሆኑ ግለሰቦችና 11 አመራሮች በሕግ እንዲጠየቁ ተደርጓል ብለዋል።


በኮንሶና ኧሌ በነበረው ግጭት እንዲሁም በስልጤ ዞን ለመቀስቀስ ተሞክሮ በነበረው የሐይማኖት ግጭት ምክንያት የተጠረጠሩ ግለሰቦችም በቁጥጥር ሥር የማዋል ሥራም እንዲሁ እየተከናወነ እንደሚገኝ አመላክተዋል።


በክልሉ በየአካባቢው ህዝቦች የሚነሱ የአደረጃጀት ጥያቄዎች ለግጭት መንስኤ ሊሆኑ አይገባም ያሉት አቶ ርስቱ እነዚህን አጀንዳዎች ተጠቅመው ክልሉን ለማወክ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ላይ የማያዳግም እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል ብለዋል።

ለዚህም የፀጥታ አካላት ብቻ ሳይሆኑ የፖለቲካ አመራሩም በቁርጠኝነት መታገልና ህዝቡን የማንቃት ሥራ መስራት እንዳለበት ነው ያስረዱት።


ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም