በሀዋሳ የዘመን መለወጫ በዓልን አስመልክቶ ለአረጋዊያንና ለጎዳና ተዳዳሪዎች ድጋፍ ተደረገ

119
ሀዋሳ ጳግሜ 4/2010 መጪው የዘመን መለወጫ በዓል ምክንያት በማድረግ በሀዋሳ ከተማ ለሚኖሩ 250 አረጋዊያንና የጎዳና ተዳዳሪዎች የምሳ ግብዣና የአልባሳት ድጋፍ ተደረገ፡፡ የሃዋሳ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ስኳሬ ሹዳ በዚህ ወቅት " የታሰሩትን፣ የታመሙትን በመጠየቅና ያዘኑትን በማጽናናት   ከጎናቸው መሆናችን ማሳየት አለብን " ብለዋል፡፡ በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተጀመሩትን የበጎ አድራጎት ስራ በመደገፍ በዓሉን ከአረጋዊያንና ከጎዳና ተዳዳሪዎች ጋር ለማሳለፍ ወስነው ድጋፉን ማመቻቸታቸውን አመልክተዋል፡፡ ምክትል ከንቲባው ጎዳና ላይ የወደቁ ወገኖችንንና ቤታቸው የተጎዳባቸው አቅመ ደካሞችን የመደገፍ ስራ እንደሚቀጥል ጠቅሰው እርስ በርስ መተጋገዝና መደጋገፍ  ካለ ለሁሉም የሚበቃ ሃብት አለ ነው ያሉት፡፡ ድጋፍ ከተደረገላቸው ወይዘሮ ማታቴ መስቀሌ በሰጡት አስተያየት መንግስት የተቸገሩትን በመፈለግ ባደረገላቸው ድጋፍ መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡ የጎዳና ተዳዳሪው ታዳጊ ተረፈ በቀለ በበኩሉ " ከጓደኞቼ ጋር በልቼ ጠጥቼ ጠግቤያለሁ " ብሏል፡፡ በአዲሱ ዓመት  ከጎዳና ተዳዳሪነት ለመውጣት እንደሚፈልግም  ተናግረዋል፡፡ እድሜያቸው 77 ዓመት እንደሆነ የገለጹት አቶ ዳረጎ ዳልቻ ለረጅም ዓመታት በአናጺነት ሙያ ሲተዳደሩ ባጋጠማቸው ህመም ላለፉት አራት ዓመታት ያለስራ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡ አሁን በዓሉን አስመልክቶ በተደረገላቸው ድጋፍ መደሰታቸውን ገልጸው ጠያቂና አስታዋሽ አለኝ የሚል ስሜት እንዳሳደረባቸው ተናግረዋል፡፡ የክልሉና የሃዋሳ ከተማ አመራሮች፣ የከተማው ወጣቶች ፌዴሬሽን የጎዳና ተዳዳሪዎችና አረጋዊያን ምሳ የጋበዟቸው ሲሆን በከተማው ወጣቶች የተሰበሰቡ አልባሳትም ተከፏፍሏቸዋል፡፡                            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም