ወደ አሰብ ወደብ የሚወስደውን መንገድ ለመጠገን ዝግጅት እየተደረገ ነው

155
ሰመራ ጳግሜ 4/2010 የአሰብ ወደብን ለመጠቀም የሚያስችል የመንገድ ጥገና ስራ ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ፡፡ የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ የመንገድና ሎጀስቲክ ኃላፊዎች ከሰመራ እስከ ቡሬ ድረስ የሚገኘውን መንገድ ትናንት ጎብኘተዋል፡፡ በጉብኝቱ ማጠቃለያ  የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስለጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሃብታሙ ተገኝ እንዳሉት የአሰብ ወደብን ለኢትዮጵያ ገቢና ወጪ ንግድ ለመጠቀም የመንገድ ስራ ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡ ከዲችኦቶ-አሌደአር ከተማ  64 ኪሎ ሜትር የሚሆነው መንገድ በኮንክሪት አስፓልት ደረጃ በ2008ዓ.ም. ግንባታው ተጀምሮ በአብዛኛው እየተጠናቀቀ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ቀሪው  ከኤሊደአር- ቡሬ የሚደርሰው 71 ኪሎ ሜትር መንገድ  በኮንክሪት አስፓልት ደረጃ ለመስራት መታቀዱን ገልጸው አሁን ግን አሰብ ወደብን ለመጠቀም የሚስችል የጥገና ስራ ለመጀመር ተቋራጩ ማሽኖችን እያስገባ ነው፡፡ የጥገና ስራውም ሶስት ወራት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ አጠናቆ ለአገልግሎት ለማዋል የሚደረገው ዝግጅት ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ የሁለቱ ሀገራት ልኡካን ቡድን እስከ ቡሬ ድረስ ባደረጉት ምልከታ ለትራንስፖርት ምቹ ከማድረግ አንጻር ጥገና የሚስፈልጋቸው ቦታዎች ቢኖሩም የአሰብ ወደብን ለመጠቀም መሰረታዊ ሊባል የሚችል ችግር አለመኖሩን ማረጋገጣቸውን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡ የኤርትራ ባህር ትራንስፖርት ባለስለጣን ዋና ዳይሬክተርና የልኡካን ቡድኑ አባል አቶ መኮንን አበራ በበኩላቸው  የሁለቱ ሀገራት በቅርቡ ባደረጉት የሰላም ስምምነት መሰረት  ያላቸውን ሃብት በጋራ በመጠቀም ተጋግዘው  ለማደግ መግባባት ላይ መድረሳቸውን አስታውሰዋል፡፡ በኤርትራ በኩል የአሰብ ወደብን የኢትጵያን  ወጪና ገቢ ንግድ ለማስተናገድ የሚያስፈልጉ ቅድመ-ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን ገልጸው " እስከ ኢትጵያ ድንበር ድረስ የሚገኘው የአስፓልት መንገድም ለአገልግሎት ዝግጁ ነው " ብለዋል፡፡ ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ መንግስት የአሰብ ወደብን ለመጠቀም የጀመረው እንቅስቃሴ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ከወደቡ ጋር በሚያገኘው መንገድ በአብዛኛው ጥሩ ቢሆንም  አልፎ አልፎ ጥገና የሚያስፈልጋቸው  እንዳሉ  በመስክ ምልከታው ወቅት ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል፡፡ የጥገናው ስራ በአጭር ጊዜ ወስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት ማብቃት እንደሚቻልም ጠቁመዋል፡፡ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጀስትክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሮባ መገርሳ  ሁለቱ ሀገራት በቅርቡ በደረሱበት ስምምነት መሰረት ኢትዮጵያ በአሰብ ወደብ በኩል ሊስተናገዱ የሚችሉ የእቃዎችን ዓይነትና መጠን ግምት የመለየት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዚህም የመርከቦች ስምሪት ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝና ወደቡን ለመጠቀም የሚያግዝ  ከተለያዩ ሚኒስትር መስሪያ ቤቶች የተወጣጡ የኮሜቴ አባላት የጋራ እቅድ አውጥተው እየሰሩ መሆኑን አመልክተዋል፡፡        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም