በሃዋሳ ከተማ በ339 ሚሊዮን ብር ወጪ የአስፓልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ተጀመረ

155

ሀዋሳ ግንቦት 18/2014 (ኢዜአ) በሀዋሳ ከተማ ቱላ ክፍለ ከተማ በ339 ሚሊዮን ብር ወጪ የ2 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ የአስፓልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ሥራ ተጀመረ።

የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ በቱላ ክፍለ ከተማው "ዳቶ" ቀበሌ የአስፋልት መንገድ ሥራውን ዛሬ በይፋ አስጀምረዋል።

ከንቲባው እንዳሉት የሃዋሳ ከተማ በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን ስፋትና እድገት የሚመጥን የመሰረተ ልማት በመገንባት የከተማውን ተወዳዳሪነት ደረጃ የሚያስቀጥሉ ልማቶች አስፈላጊ ናቸው ብለዋል።

በከተማዋ በሁሉም አካባቢዎች ደረጃቸውን የጠበቁ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ዛሬ የግንባታ ስራው የተጀመረው የአስፋልት ኮንክሪት መንገድም "ዳቶ" እና "ጨፌ" የተባሉ ቀበሌዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግና ለግንባታውም 339 ሚሊዮን ብር መመደቡን ተናግረዋል።

የከተማ አስተዳደሩ የነዋሪዎችን የልማት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመፍታት እየሰራ መሆኑንም ከንቲባው ገልጸዋል።

በአስተዳደሩ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ታሪኩ ታመነ በበኩላቸው፣ የሚገነባው መንገድ 2 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር ርዝመት እንዳለው ገልጸዋል።

ግንባታው በሁለት ምዕራፎች ተከፍሎ እንደሚከናወንና በሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ አስፈላጊው ክትትልና ቁጥጥር እንደሚደረግ ተናግረዋል።

በቅድመ ዝግጅት ምዕራፍም መንገዱ የሚነካቸው ቤቶችን እንዲሁም የመብራት፣ የቴሌ እና የውሃ መስመሮችን የማንሳት ሥራ መጠናቀቁንም ኃላፊው አስታውቀዋል።

አቶ ታሪኩ እንዳሉት ከተማ አስተዳደሩ የ90 ቀናት የሥራ ዕቅድን መነሻ በማድረግ በርካታ የልማት ፕሮጀክቶችን እያከናወነ ይገኛል።

በአሁን ወቅት የ20 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ፣ አዳዲስ የመንገድ ከፈታ ሥራዎች፣ የፍሳሽ ማስወገጃ ቦዮች ሥራ በከተማዋ እየተከናወኑ መሆናቸውን ለአብነት በመጥቀስ ።

መንገድ ስራውን የሚያከናውነው"ይርጋለም ኮንስትራክሽን”  ባለቤት ኢንጂነር ዘላለም ወልደአማኑኤል በበኩላቸው "የግንባታ ስራውን በተያዘለት ጊዜና የጥራት ደረጃ ሰርቶ ለማጠናቀቅ ጥረትእናደርጋለን ብለዋል።

ለሥራው ስኬታማነት ከሚመለከታቸው አካላትና ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በመተባበር እንደሚሰሩም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም