የየካ ክፍለ ከተማ ደንብ ማስከበር ጽህፈት ቤት ከቅጣትና ከተወረሱ ንብረቶች ሽያጭ የሰበሰበውን 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ገቢ አደረገ

185

ግንቦት 18/2014/ኢዜአ/ በአዲስ አበባ የየካ ክፍለ ከተማ ደንብ ማስከበር ጽህፈት ቤት ከቅጣትና ከተወረሱ ንብረቶች ሽያጭ የሰበሰበውን 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ለከተማ አስተዳደሩ ገቢ ማድረጉን ገለጸ።

የየካ ክፍለ ከተማ ደንብ ማስከበር ጽሕፈት ቤት የሚያከናውናቸውን ተግባራት የሚያሳይ የፎቶ አውደ- ርዕይም "የደንብ ጥሰትን በጋራ እንከላከል" በሚል መሪ ሃሳብ በዛሬው ዕለት ተካሂዷል።

የየካ ክፍለ ከተማ ደንብ ማስከበር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኮማንደር አስፋው የሺዳኜ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ባለፉት አሥር ወራት በተለያዩ ደንብ ጥሰት ተግባራት ላይ እርምጃ ተወስዷል።

የገንዘብ ቅጣቱም በዋነኝነት የተሰበሰበው ከሕገ-ወጥ መሬት ወረራና መስፋፋት፣ ፈቃድ የሌለው ግንባታና  የጎዳና ላይ ንግድ መሆኑን ጠቁመዋል።

ጎን ለጎንም ከሕገ-ወጥ ደረቅ ቆሻሻና ፍሳሽ አወጋገድ፣ ከሕገ-ወጥ እርድና ማስታወቂያ፣ ከአዋኪ ድርጊቶችና የመንገድ አጠቃቀም ሥርዓት ጋር በተያያዘም የገንዘብ ቅጣት መሰብሰቡን ገልጸዋል።

በአጠቃላይ ጽሕፈት ቤቱ ከቅጣትና ከተወረሱ ንብረቶች ሽያጭ የተሰበሰበ 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ገቢ መደረጉን ነው የጠቆሙት።

እርምጃ ከመውሰድ ባሻገር ለኅብረሰተቡ የግንዛቤ ማስጨበጫና የቅድመ-መከላከል ሥራ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በየካ ክፍለ ከተማ የሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዮሐንስ ስዩም በበኩላቸው፤ በቀጣይ ደንብ የሚጥሱትን ከቅጣት ባለፈ በሕግ ተጠያቂ የሚሆኑበት ሥርዓት ላይ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ይህም የደንቦች ጥሰትን እንደሚቀንስና በተደጋጋሚ ጥፋት ለሚያጠፉት ጭምር ማስተማሪያ ይሆናል ነው ያሉት።

ይህንንም ለመተግበር የሰላምና ፀጥታ አስተዳደር፣ ከደንብ ማስከበር ጽሕፈት ቤት፣ ከፌደራል ፖሊስና  ዐቃቤ ሕግ ጋር በመሆን የእርምጃ ሥራ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም