በዞኑ በአጥፊዎች ላይ የተጀመረው ህግ ማስከበር ዘመቻ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ

168

ደብረ ብርሀን፤ ግንቦት 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) በሰሜን ሸዋ ዞን ህዝብ የማይንገላታበትና ተረጋግቶ የልማት ስራዎችን መከወን እንዲችል በአጥፊዎች ላይ የተጀመረው ህግ ማስከበር ዘመቻ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ገለፁ።

በተጀመረው የህግ ማስከበር ዘመቻ ተጨባጭ ለውጥ በመምጣቱ በዞኑ አንጻራዊ ሰላም መስፈኑንም ጠቁመዋል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ገብረፃድቅ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት በአንዳንድ አጥፊ ግለሰቦችና ቡድኖች እየደረሰ ያለው የፀጥታ ችግር እልባት ለመስጠት ጠንካራ ህግ የማስከበር ስራ እየተከናወነ ነው።

በዚህም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ከህዝብ ጋር ባካሄዱት ምክክር የህግ የበላይነት እንዲከበር ህብረተሰቡ ለመንግስት ጠንከር ያለ ጥያቄ ሲያቀርብ መቆየቱን አስታውሰዋል።

በዚህም በተቀናጀ መንገድ የህብረተሰቡን ጥያቄዎች ለመመለስ ከግንቦት 1/2014 ዓም ጀምሮ ህግ ማስከበርና አጥፊዎችን በቁጥጥር ስር የማዋል ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

እየተካሄደ ባለው ህግ ማስከበር እንቅስቃሴም በስርቆት፣ በሰው መግደል፣ በአሰገድዶ መድፈር፣ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር፣ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ በማህበራዊ ሚዲያ የሀሰት መረጃ በማሰራጨትና መሰል ወንጀሎች የተጠረጠሩ 302 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልፀዋል።

መንግስት ህብረተሰቡን በማስተባበር እየወሰደ ባለው የህግ ማስከበር እርምጃም አጥፊዎችን በማጋለጥና በመጠቆም የህብረተሰቡ ተሳትፎ ከፍተኛ መሆኑን አመልክተዋል።

ባለፉት ሳምንታት በተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻም ተጨባጭ ለውጥ በመምጣቱ በዞኑ አንጻራዊ ሰላም መስፈኑን ጠቁመው፤ ከአጎራባች ክልሎችና ዞኖች ጋር በቅንጅት አየተሰራ እንደሆነም ተናግረዋል።በህግ ቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎች ጉዳያቸው በህግ እየታየ መሆኑን ጠቅሰው፤ ህግ የማስከበር ጥረቱም የበለጠ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ዋና አስተዳዳሪው አስታውቀዋል።

አሸባሪው ህወሃት ጦርነት በከፈተብን ወቅት ከመንግስት ቀለብና ትጥቅ ሳይጠይቅ ህይወቱን ለሀገርና ለህዝብ የሰጠን እውነተኛ የፋኖ አባላትን በህግ ማስከበር ሂደቱ አይካተቱም ብለዋል።

ነገር ግን በፋኖ ስም ህገ ወጥ ተግባር የሚፈጽሙ አካላትን በመረጃ ላይ ተመስርቶ በመለየት የተጀመረው የህግ ማስከበር ሂደት አሁንም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

በተሳሳተ መንገድ ለጠላት መጠቀሚያ ለመሆን የሚንቀሳቀሱ ወጣቶች ከእኩይ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ የሃገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች በመምከር የድርሻቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።

በዘመቻው ንፁሃን ዜጎች እንዳይያዙ ብሎም ከአላግባብ እንዳይንገላቱ በጥንቃቄና በተጠና መንገድ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ህብረተሰቡ ከፀጥታ መዋቅሩ ጎን በመሆን አጥፊዎችን በመጠቆምና በማጋለጥ የጀመረውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ዋና አስተዳዳሪው ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም