በዞኑ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ የሆነና በጣዕሙ የሚታወቅ ቡና ለማምረት እየተሰራ ነው

159

ሻሸመኔ ግንቦት18/2014 /ኢዜአ/ --- በጥራቱ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ የሆነና በጣዕሙ የሚታወቀውን ቡና ለማምረት በትኩረት እየሰራ መሆኑን የምዕራብ አርሲ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ሃላፊ ዶክተር አብዱላሂ ቤካ እንደገለጹት ነንሰቦ ወረዳን ጨምሮ ቡና የሚመረትባቸው በስድስቱ የዞኑ ወረዳዎች ውስጥ የተሻለ ጣዕም ያለው የቡና ዝርያ ይገኛል።

ይህን የቡና ዝርያ በጥራት ለማምረትና በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆን በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ነው ሃላፊው የሚናገሩት።

በዚህም ቀደም ብሎ ከኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ጋር በመተባበር ለዞኑ ግብርና ባለሙያዎች ስልጠና መሰጠቱንም አስታውሰዋል።

በዞኑ ከ44ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት በቡና የተሸፈነ መሆኑንና ከዚህ መካከል 34 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የለማው ቡና ምርት እየሰጠ መሆኑንም ዶክተር አብዱላሂ ገልፀዋል።

መጪው ክረምትም ከ10 ሚሊየን በላይ የቡና ችግኝ በ10 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ለመትከል ዝግጅት ላይ መሆናቸውን ገልጸው ያረጁ  የቡና ዛፎችን በመንቀል አዲሱን ለመትከል እንደሚሰራም ገልጸዋል።

ዘንድሮ ለተከላ የተዘጋጀው ቡና ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር  ሲነፃፀር በ950 ሺህ ብልጫ እንዳለውም አክለዋል።

እስካሁን ከ6 ሚሊየን 700 ሺህ በላይ የተከላ ጉድጓድ መዘጋጀቱን የተናገሩት ሃላፊው፣ ከ11ሺህ በላይ  አርሶ አደሮች እንደሚሳተፉም ነው የገለፁት።

የሚተከሉ የቡና ችግኞችም በምርምር የወጡና ምርታማነታቸው የተረጋገጠ ሲሆን አንድ አርሶ አደር  በአማካይ 890 ችግኞችን እንደሚተክልም ተናግረዋል።

ልዩ ጣዕም ያለው  የነንሰቦ ወረዳ ቡናን ይበልጥ በማስፋፋት አርሶ አደሮቹ ቡናውን በማምረት ለሀገሪቱ የገቢ ምንጭ እንዲያስገኙ እየተሰራ መሆኑን  አክለዋል።

በነንሰቦ ወረዳ መንዶዬ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ካሊድ አማን ቡና ማምረት ከጀመሩ ከአስር ዓመት በላይ ሆኗቸዋል።

ባለፈው ዓመት 3 ሄክታር  አዲስ መሬት ላይ ቡና እንዳለሙ ገልፀው፣ ዘንድሮ ያረጁትን የቡና ተክል በመንቀል አንድ ሄክታር ላይ ተጨማሪ ቡና ለመትከል መዘጋጀታቸውን ነው የተናገሩት።

እስካሁንም 400 ጉድጓድ እንዳዘጋጁና፣ በአጠቃላይ ከቡና በሚያገኙ ገቢ ቤተሰባቸውን በጥሩ ሁኔታ  እያኖሩ መሆኑን ተናግረዋል።

የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሰዒድ አሊ በበኩላቸው ቡና ማምረት ከጀመሩ አምስት አመታትን ያስቆጠሩና በ3 ሄክታር መሬት ላይ እንደሚያመርቱ ገልፀዋል።

ባለፈው ዓመት 400 የቡና ችግኝ እንደተከሉና ለመጪው ክረምትም ግማሽ ሄክታር አዲስ እና ነባር መሬት ላይ ለመትከል እንደተዘጋጁ ተናግረዋል።

እስካሁንም 350 የመትከያ ጉደጓድ ማዘጋጀታቸውን አክለዋል።

"የቡና ዋጋ እየተሻሻለ በመምጣቱ እኔም የግብርና ባለሙያዎች የሚሰጡኝን ምክርና የሚያደርጉልኝን ድጋፍ ተጠቅሜ ይበልጥ ተጠቃሚ ለመሆን እሰራለሁ" ብለዋል።

"ከቡና ግብይት ከ1 ሚሊየን ብር በላይ ካፒታል ስላስመዘገብኩ ወደ ኢንቨስትመንት ለመሻገር ፍቃድ አግኝቻለሁ" ሲሉም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም