የተዛቡ የታሪክ ትርክቶችን በማስተካከል የኢትዮጵያን መፃኢ ጉዞ የተሻለ ማድረግ ያስፈልጋል

128

ግንቦት 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) የተዛቡ የታሪክ ትርክቶችን በማስተካከል የኢትዮጵያን መፃኢ ጉዞ የተሻለ ማድረግ እንደሚያስፈልግ የታሪክ ምሁራን ገለጹ።

የኢትዮጵያ የታሪክ ባለሙያዎች ማህበር ከሰላም ሚኒስቴርና ዴስትኒ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር "ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር የታሪክ ሚና" በሚል መሪ ኃሳብ የምክክር መድረክ አካሂዷል።

በመድረኩም የተዛቡ የታሪክ ትርክቶችን በማስተካከል የኢትዮጵያን ሉዓላዊ አንድነት አስጠብቆ ለማስቀጠል የሚረዱ ኃሳቦች ተዳሰዋል።

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህርና የታሪክ ኢምሬትስ ፕሮፌሰር ሹመት ሲሻኝ፤ አገርን በማጽናት ታሪካዊ አንድነትን የሚያስቀጥሉ ተግባራትን ማከናወን ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ባሳለፈቻቸው የአስተዳደር ዘመናት ዘመናዊ የአገረ መንግሥት ሽግግር ባለመካሄዱ በአገራዊ ምንነትና ግንባታ ሂደቶች በተዛቡ ትርክቶች እጅ እንዲወድቅ ማድረጉን ገልጸዋል።

የአገረ መንግሥት ግንባታ ሂደቱም ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ይልቅ በውጭው ዓለም በተቃኘና ባልተጣጣመ የማርክሲስት ሌኒንስት ርዕዮተ-ዓለም ተጽዕኖ እንዲወድቅ ማድረጉን አንስተዋል።

ይህም ኢትዮጵያዊያንን ለዘመናት አስተሳስረው ያቆዩ ባህላዊና ታሪካዊ አንድነቶችን በማግለል ለተሳከረ የትርክት ርዕዮተ-ዓለም እንዲጋለጡ ማድረጉን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያዊያን የሰመረ የወንድምና እህትማማችነትም በጊዜ ሂደት ወደ መፋለስ እንዲሸጋገር በማድረግ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳረፈ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ተራማጅ የሆነ አገረ መንግሥት በመመስረት ፋንታም ትውልዱ "በጠባብ ማንነት" የተወጠረ የታሪክ አረዳድን እንዲይዝ እያደረገ እንደሚገኝ አመላክተዋል።

ኢትዮጵያዊያን ሰፊ የማንነት ጥላና የወደፊቱን እጣ ፋንታቸውን የመወስን እድል ኖሯቸው ሳለ የልዩነትና የማያገናኝ የትርክት መንገድ ሲተረክላቸው መቆየቱን ተናግረዋል።

ይህኑ የተዛባ የታሪክ ትርክትን በማስተካከልም የኢትዮጵያን መፃኢ ጉዞ የተሻለ አድርጎ ለመጪው ትውልድ የምትሆን የተሻለች አገርን ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ መክረዋል።

በተዛቡ የታሪክ ትርክቶች የሚፈጠሩ ችግሮችን በዘላቂነት እልባት ለመስጠትም ምሁራን ከዳር ተመልካችነት በመላቀቅ የመፍትሄ አካል የሚሆኑ ኃሳቦችን ማፍለቅ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

በዲላ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል የታሪክና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ረዳት ፕሮፌሰሩ አብዱ መሃመድም፤በተዛቡ ትርክቶች ሳቢያ የኢትዮጵያ ታሪክ ከአስተማሪነቱ ይልቅ አጨቃጫቂነቱ ጎልቶ እየተመጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ታሪክ ያለፉትን ክስተቶች በዛሬና ነገ ለማየት የሚረዳ ሁነኛ መሳሪያ መሆኑን ጠንቅቆ በማወቅም ለተሻለ ነገ የሚበጅን ኃሳብ አጉልቶ ማስተጋባት እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።

በትናንት፣ዛሬና ነገ ያለውን ጥብቅ ቁርኝት በመገንዘብም በታሪካዊ ዑደቶች የታለፉ መልካምና መጥፎ ሁነቶችን በመለየት መልካሙን ማስፋት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያዊያንም ትናንት ከታለፉ በጎና መጥፎ ነገሮች ትምህርት ወስደው ለተሻለ ነገ የሚበጁ ኃሳቦችን ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።አንባቢ ትውልድን በመፍጠርም ለአገረ መንግሥት ቀጣይነት የሚበጅን ምክንያታዊነት ማጎልበት እንደሚያስፈልግ መክረዋል።

በኢትዮጵያ በተለያዩ የፖለቲካና የኃሳብ መሪዎች እንዲሁም የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል በመሠረታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ያለውን የኃሳብ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ለማርገብና አገራዊ ምክክር መቋቋሙ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም