የብሄር፣ ቋንቋና የሃይማኖት ልዩነት የአብሮነታችን ፈተና ሆኖ አያውቅም

105

ግንቦት 17/2014/ኢዜአ/ የብሄር፣ ቋንቋ፣ ማንነትና የሃይማኖት ልዩነት የሁለንተናዊ ትብብር መሰረት እንጂ የአብሮነታችን ፈተና ሆኖ አያውቅም ሲሉ በምንጃር ሸንኮራና ግምቢቹ ወረዳ ተጎራባች አርሶ አደሮች ተናገሩ።

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ እና በአሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ግምቢቹ ወረዳ ተጎራባች ቀበሌዎች ማህበረሰቡ  በደም የተሳሰረ፣ በመስተጋብሮች የዳበረና በግብይት የተቆራኘ ነው።

የአካባቢው ነዋሪዎች በአማርኛና ኦሮምኛ ቋንቋዎች እየተግባቡ ተዛምደው፣ ተዋልደውና በጥብቅ ማህበራዊ እሴት ተጋምደው ይኖራሉ።

በምንጃር ሸንኮራ የተመረተውን በግምቢቹ ገበያ፤ የግምቢቹን ደግሞ ለምንጃር ገበያ በማቅረብ ይሸማመታሉ።

በዕድር፣ ሰርግና ተዝካርም ሆነ ሌሎች ማህበራዊ ክዋኔያቸው ከጥንት አስከ ዛሬ ያልተለያዩ ጥብቅ ቁርኝትና የዳበረ እሴት ያላቸው ማህበረሰቦች ናቸው።

የኢዜአ ሪፖርተር በአካባቢው ተገኝቶ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እንደሚሉትም የሁለቱ ክልል አጎራባች ህዝቦች ትስስር ላይፈታ ተቋጥሮ፣ ላይበጠስ ተጋምዶ ዘመናትን ተሻግሯል።

የአካባቢው ነዋሪዎች በሰርግም ሆነ በለቅሶ የማይለያዩ በደቦ እያረሱ፣ በአጨዳና ምርት አሰባሰብ እየተጋገዙ በመኖር በቆየ ባህላቸው ይታወቃሉ።

የብሄር፣ ቋንቋ፣ ማንነትና የሃይማኖት ልዩነት የሁለንተናዊ ትብብር መሰረት እንጂ የአብሮነት ፈተና አለመሆኑንም ያስረዳሉ።

የእህል ዘር መለዋወጥ እንጂ በዘር ልዩነት የመተያየት ሀሳብ ኑሮን አያውቅም ይላሉ የአካባቢው ነዋሪዎች።

በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ዱበቱ ቀበሌ ነዋሪዎች መካከል አቶ ግርማ ታዬ፣ አቶ አየለ እሸቱና ወጣት ከበደ ገመቹ የማይጋሩት ማህበራዊ መስተጋብር እንደሌለ ይናገራሉ።

በህዝብ ዘንድ ልዩነት ወደ መከፋፈልና ግጭት እንዲያመራ በተለይም አንዳንድ ተማሩ የሚባሉና የፖለቲካ አላማ ያላቸው አካላት ለመለያየት እየሰሩ መሆኑን እንረዳለን ብለዋል።

እንዲህ አይነት እኩይ ዓላማ አንግበው የሚሰሩ ቢኖሩም የማህበረሰቡ ጥብቅ ቁርኝትና አብሮነት በዘላለማዊነቱ እንደሚቀጥል በጽኑ ያምናሉ።

በሌሎች አካባቢዎች የብሄር ወይም ሌሎች ልዩነቶችን መሰረት በማድረግ ተከሰቱ በሚባሉ ግጭቶች በሚሰሙት ነገር እንደሚያዝኑ ይናገራሉ።

የጦርነት ቅስቀሳና የእርስ በርስ ግጭት ለአገርም ለህዝብም የማይጠቅም በመሆኑ በጋራ ሰርተን አምርተን ለልጆቻችን የሚጠቅም አገር መገንባት አለብን ብለዋል።

'ኢትዮጵያ አንድ ናት፤ እርስ በርስ መባላት የለብንም፣ የጦርነቱ እልቂት ትርፍ የለውም' ያሉት ነዋሪዎቹ ኦነግ ሸኔን ጨምሮ ግጭት ቀስቃሾች ተጠያቂ መሆን አለባቸው ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም