በክልሉ ሲካሄድ የቆየው የታዳጊ ወጣቶች የኦሎምፒክ ስፖርቶች ውድድር በሸካ ዞን አሸናፊነት ተጠናቀቀ

78

ሚዛን ግንቦት 17/2014 (ኢዜአ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ላለፉት አራት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የታዳጊ ወጣቶች የኦሎምፒክ ስፖርቶች ውድድር በሸካ ዞን የአጠቃላይ አሸናፊነት ተጠናቀቀ ።

በሚዛን አማን ከተማ በእግር ኳስ፣ እጅ ኳስ፣ አትሌቲክስ፣ ጠረጴዛ ቴኒስ፣ ወርልድ ቴኳንዶና ውሹ የስፖርት አይነቶች ሲካሄድ የቆየው ስፖርታዊ ውድድር ትናንት ማምሻውን ተጠናቋል።

ከ18 ዓመት በታች የታዳጊ ወጣቶች የኦሎምፒክ   ስፖርቶች  ውድድር   የሸካ ዞን  10 ወርቅ፣ 12 ብርና 5 የነሐስ ሜዳሊያ በድምሩ 27 ሜዳሊያዎችን በማግኘት በበላይነት ማጠናቀቅ ችሏል።

የኮንታ ዞን 10 የወርቅ፣ 3 የብርና 7 የነሐስ ሜዳሊያ  እንዲሁም የቤንች ሸኮ  ደግሞ 7 ወርቅ፣ 7 የብር ፣ 6  የነሐስ  ሜዳልያ በማግኘት እንደቅደመ ተከተላቸው 2ኛ እና 3ኛ ደረጃን በመያዝ  ውድደሩን አጠናቅቀዋል።

ለአሸናፊዎቹ የተዘጋጀውን የዋንጫና የሜዳሊያ ሽልማት ያበረከቱት የክልሉ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፋንታሁን ብላቴ  ናቸው።

አቶ ፋንታሁን እንዳሉት ውድድሩ በስፖርታዊ ጨዋነትና በወንድማማችነት መንፈስ ተካሂዶ በመጠናቀቁ መደሰታቸውን ገልጸው  በማንኛውም  የስፖርት  ውድድሮች  ኢትዮጵያዊ ወንድማማችነትን ማጎልበት እንደሚገባ አስታውቀዋል።

በውድድሩ በሀገር  አቀፍ ደረጃ  ከ18 ዓመት  በታች የታዳጊ ወጣቶች   ውድድር ላይ ክልሉን  የሚወክሉ ስፖርተኞች የተመረጡበት መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይ ሀዋሳ ላይ በሚካሄደው ሀገር አቀፍ ስፖርታው ውድድር ላይ የሚሳተፉ ስፖርተኞች በሚያስመዘግቡት ውጤት በአፍሪካ ኦሎምፒክ ላይ ሀገርን ወክለው የሚወዳደሩበት እድል ለማግኘት ከወዲሁ ጠንክረው መዘጋጀት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አህመዲን አወል በበኩላቸው በሁሉም የስፖርት መስክ ምርጥስፖርተኞችን ለማፍራት የተጀመረው ጥረት  ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

በተለይ በክልሉ የሚገኙ ታዳጊ ስፖርተኞችን አቅም በመገንባት ውጤታማ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።