በአፋር ክልል የልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ) መከላከያ ክትባት ዘመቻ ተጀመረ

122

ግንቦት 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአፋር ክልል የልጅነት ልምሻ(ፖሊዮ) መከላከያ ክትባት ዘመቻ ዛሬ ተጀምሯል።

ትናንት በሎጊያ ጤና ጣቢያ በተጀመረው ዘመቻ እድሜያቸው ከአምስት አመት በታች የሆኑ ከ187 ሺህ በላይ ሕጻናቶች እንደሚከተቡ ተገልጿል።


የአፋር ክልል ማህበረሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ፈረጅ ረቢሳ በ2014 ዓ.ም በክልሉ የፖሊዮ ክትባት ሲሰጥ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው ብለዋል።


ሁለተኛ ዙር ክትባቱ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች፣ በጤና ተቋማቶችና ተፈናቃዮች በሚገኙበት ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎችን ጨምሮ ቤት ለቤት እንደሚሰጥ ገልጸዋል።


እስከ ግንቦት 19 ቀን 2014 ዓ.ም በሚቆየው ዘመቻ እድሜያቸው ከአምስት ዓመት የሆኑ 187ሺ በላይ ሕጻናቶች ይከተባሉ ብለዋል።


ወላጆች ልጆቻቸውን ከልጅነት ልምሻ በሽታ ለመታደግ ክትባቱን እንዲያስከትቡ ጥሪ ያቀረቡት ዳይሬክተሩ አመራሮች፣የሃይማኖት አባቶችና የማህበረሰብ መሪዎች ለክትባቱ ውጤታማነት ትብብር እንዲያደርጉ አሳስበዋል።


ፖሊዮ (ፖሊዮሚለትስ) ተብሎ የሚጠራው የልጅነት ልምሻ በሽታ እ.አ.አ በ1800 አካባቢ እንደተከሰተ የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል።


የልጅነት ልምሻ በዋናነት የሚያጠቃው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናትን ሲሆን ከሰው ወደ ሰው በንክኪ፣በቫይረሱ በተበከለ ምግብ እና ውሃ አማካኝነት ወደ ሰውነት እንደሚገባ የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በሽታው አይነት 1፣ አይነት 2 እና አይነት 3 በመባል ይታወቃል።


በሽታው በዘላቂነት የሰውን የአካል ቅርጽ በመቀየር ለአካል ጉዳት የሚዳርግ ሲሆን በሽታው ለሞትም እንደሚያደርስ ይገለጻል።


በኢትዮጵያ ፖሊዮን ለመከላከል ሁለተኛ ዙር አገር አቀፍ የክትባት ዘመቻ ሚያዚያ 9 ቀን 2014 ዓ.ም በአማራ ክልል የተጀመረ ሲሆን፤በክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ዘመቻው እየተካሄደ ይገኛል።


ኢትዮጵያ ለመጨረሻ ጊዜ የዋይልድ ፖልዮ ቫይረስ ሪፖርት አድርጋ የነበረው በጥር ወር 2006 ዓ.ም የነበረ ሲሆን በ2009 ዓ.ም ከዋይልድ ፖሊዮ ነጻ መሆኗን በአፍሪካ ደረጃ የተቋቋመ ኮሚቴ እንዳረጋገጠና በአሁኑ ሰዓት የዋይልድ ፖሊዮ በሽታ በአፍሪካ አህጉርም ለመጥፋቱ ማረጋገጫ ተሰጥቶ እንደነበር የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ገልጿል።


ይሁንና በአሁኑ ጊዜ በአጎራባች አገሮች ሲዘዋወር የቆየ በክትባት እጥረት የሚመጣ የፖሊዮ ቫይረስ ከታህሳስ ወር 2011 ዓ.ም ጀምሮ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ መኖሩ ከሰው እና ከአካባቢ ከተወሰዱ ናሙናዎች በተሰራ ቅኝት ማረጋገጥ መቻሉን አመልክቷል።


ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️