በጋምቤላ ክልል የተገልጋዩን ፍላጎት ለማርካት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተገለጸ

131

ጋምቤላ፤ ግንቦት 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል ቀልጣፋና ዘመናዊ የሲቪል ሰርቪስ የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት የተገልጋዩን ፍላጎት ለማርካት ሊሰራ እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ አሳሰቡ።

በክልሉ የተቀናጀ የሲቪል ሰርቪስ መረጃ አያያዝ ስርዓት ፕሮጀክት ማስጀመሪያ መረሐ ግብር ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተካሂዷል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በመርሐ ግብሩ ላይ እንደገለጹት እያደገ የመጣውን የተገልጋዩን ፍላጎት ለማርካት ቀልጣፋና ዘመናዊ የሲቪል ሰርቪስ ስራዓት መዘርጋት ያስፈልጋል።

በተለይም በክልሉ የሚታዩ የኪራይ ሰብሳቢነትና የብልሹ አሰራር ችግሮችን በመቅረፍ ለማህበረሰቡ ፍትህዊና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ተቋማቱ ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።

አሁን ላይ ያለውን ኋላ ቀር የሰው ሀብት መረጃ አደረጃጀትና አሰራር ስራዓትም ማዘመን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

አዲስ ለሚጀመረው የሲቪል ሰርቪስ የተቀናጀ የመረጃ አያያዝ ስርዓት ፕሮጀክት ውጤታማነት በየደረጃው የሚገኙ ተቋማት በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ኛሞች ጊል በበኩላቸው ቢሮው የክልሉ የመንግስት ተቋማትን አደረጃጀትና አሰራር በማዘመን ለተገልጋዩ ህብረተሰብ ቀልጣፍ አገልግሎት ለመስጠት እየሰራ ነው።

ዛሬ የተጀመረው የተቀናጀ የሲቪል ሰርቪስ መረጃ አያያዝ ስርዓት ፕሮጀክት ዘርፉን ለማሻሻል እየተከናወኑ ያሉት ስራዎች አካል መሆኑን ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ የአሰራርና የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓቱን ከማዘመኑም በተጨማሪ የሰው ሀብት ቅጥር፣ እድገት፣ ዝውውርና ስንብትን በመረጃ ቋት በመያዝ ያልተገቡ ክፍያዎችን ያስቀራል ብለዋል።

በፕሮጀክቱ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ላይ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች መገኘታቸው ተመላክቷል።