መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ለ 439 መምህራን የጋራ መኖሪያ ቤት ቁልፍ አስረከበ

87


ግንቦት 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የተሻለ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር ለ439 መምህራን ያስገነባውን የጋራ መኖሪያ ቤት ቁልፍ አስረከበ፡፡


የዕድሉ ተጠቃሚ የሆኑት የዩኒቨርሲቲው መምህራን በበኩላቸው የጋራ መኖሪያ ቤት ማግኘታቸው፤ የመማር ማስተማሩን ሂደት በተረጋጋ ሁኔታ ለመከወን ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡


በቁልፍ ርክክብ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር አህመድ ከሊል እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ሂደቱን ምቹ በማድረግ ጥራት ያለው ትምህርት ለመስጠት የሚያስችሉ ስራዎች እየሰራ ይገኛል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ለጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታው ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉን የገለጹት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው የቢዝነስ ልማት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ለታ በከሬ ናቸው፡፡

ለመምህራኑ በዕጣ የተላለፈው ባለ 22 ብሎክ የጋራ መኖሪያ ቤት ስቱዲዮ፣ ባለ አንድ መኝታ፣ ባለ ሁለትና ባለ ሶስት መኝታ ያላቸው ቤቶች መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡


ቤቶቹ መምህራኑ በተቋሙ እስካሉ ድረስ በነጻ እንደሚኖሩበትም ነው የተገለፀው፡፡


ዶክተር ለታ አክለውም የቤት ድልደላን በሚመለከት የአሰራር ግድፈት እንዳይኖር የቤት ዕደላ ኮሚቴ ተዋቅሮ ግልፀኝነት በተሞላበት መንገድ ሲሰራ መቆየቱንም ተናግረዋል፡፡


የጋራ መኖሪያ ቤት ቁልፉን ከተረከቡት መምህራን መካከል አቶ ሀሰን ዴሲሶ በሰጡት አስተያየት ቤቱን ማግኘታቸው መደበኛ የመማር ማስተማር ስራቸውን ተረጋግተው ለማከናወን እንደሚያስችላቸውና ከነበረባቸው የቤት ችግር እፎይታ እንደሰጣቸው አመልክተዋል።


የኑሮ ውድነቱ ከአቅም በላይ እየሆነ በመጣበት በዚህ ወቅት ከኪራይ ቤት ወጥተው ይህንን እድል ማግኘታቸው ስራቸውን በአግባቡ ለማከናወን እንደሚረዳቸው የተናገሩት ደግሞ ሌላ የእድሉ ተጠቃሚ መምህር አብዲሳ ነገዎ ናቸው፡፡


በ1999 ዓ.ም የተቋቋመው መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ወቅት ከ20ሺህ የሚበልጡ ተማሪዎችን በተለያዩ መርሃ ግብሮች በማስተማር ላይ እንደሚገኝ ከዩኒቨርሲቲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡


ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም