በክልሉ 80 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጠ

151


ግንቦት 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) በክልሉ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ በተከናወኑ ሥራዎች 80 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሃብቶች ፈቃድ መሰጠቱን የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ፡፡

በኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ያለመ የምክክር መድረክ በኮምቦልቻ ከተማ ተካሂዷል።

የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ የኢንስትመንት በማሳደግ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት በቅንጅት እየተሰራ ነው።


ለዚህም በክልሉ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጭ በመጠቀም በተለያዩ ዘርፎች ባለሀብቶች እንዲሰማሩ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።


ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተደረገ ጥረትም 80 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ 1 ሺህ 397 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ መሰጠቱን ተናግረዋል።


ባለሀብቶቹ በወሰዱት ፈቃድ ወደ ሥራ ሲገቡ ከ252 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የሥራ እድል እንደሚፈጥሩ ገልጸው፣ፈጥነው ሥራ እንዲጀምሩ አስፈላጊው እገዛ እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል።


እንደ ኃላፊው ገለፃ ባለሀብቶቹ የኢንቨስትመንት ፍቃዱ የወሰዱት በማኑፋክቸሪንግ፣በኮንስትራክሽን፣በሆቴል ቱሪዝምና መሰል ዘርፎች ላይ ለመሰማራት ነው።


ባለፉት ዓመታት ተገንብተው ወደ ሥራ የገቡ ከ3 ሺህ 600 የሚበልጡ አምራች ኢንዱስትሪዎችም ከ75 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የሥራ እድል በመፍጠር ተጠቃሚ ማድረጋቸውን አብራርተዋል።


በክልሉ አሸባሪው ህወሓት ወረራ በፈፀመባቸው አካባቢዎች በ180 ኢንዱስትሪዎች ላይ ዝርፊያና ውድመት ማድረሱን ጠቁመው፣ በአሁኑ ወቅት 165ቱ መልሰው ተቋቁመው በከፊል ሥራ እንዲጀምሩ ተደርጓል።


ቀሪዎቹም ችግሮቻቸው ተፈትቶ ሥራ እንዲጀምሩ መንግስት በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።


የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሀብታሙ ኃይሌ በበኩላቸው በከተማው ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 29 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ መውሰዳቸውን ተናግረዋል።


ፈቃድ የተሰጣቸውም ከ8 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩ ጠቁመው፣ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮላቸው ወደ ስራ እንዲገቡ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።


በውይይቱ ተገኝተው መልእክታቸውን ያስተላለፉት የክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ እንዳሉት "ባለሀብቶችን ደግፎና ተከታትሎ በገቡት ውል መሰረት ወደ ሥራ እንዲገቡ ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት"።


ሁሉም ተግባብቶ መስራት ከተቻለ የባለሀብቶችን የተለያዩ ችግሮች መፍታት እንደማይከብድ የገለጹት አፈ ጉባዔዋ፤ ምክር ቤቱም ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።


አምራች ኢንዱስትሪዎችም ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት በተደራጀና በተጠና አግባብ ወደ ስራ ከመግባት ባለፈ ለዜጎች የሥራ እድል በመፍጠር ህብረተሰቡን መጥቀም እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።



ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም