በመንግስት በተመደበ 520 ሚሊዮን ብር 23 የመስኖ ፕሮጀክቶች አዋጭነት ጥናትና ዲዛይን እየተከናወነ ነው

239

ግንቦት 16 ቀን 2014 (ኢዜአ) በመንግስት በተመደበ 520 ሚሊዮን ብር 23 የመስኖ ፕሮጀክቶች አዋጭነት ጥናትና ዲዛይን እየተከናወነ መሆኑን የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ገለጸ።

በኢትዮጵያ የተጀመረውን በምግብ ራስን የመቻል ጉዞ ለማሳካት መንግስት የተለያዩ ተጨባጭ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል።

በዘንድሮው ዓመት ብቻ በትላልቅና አነስተኛ የመስኖ ልማት የበጋ ስንዴ ሰብል በብዙ ሺህ ሄክታር መሬት ላይ እየለማ መሆኑ ይታወቃል።

ከሚለማው ሰብል 25 ሚሊየን ኩንታል ምርት የሚጠበቅ ሲሆን በቀጣይ ዓመታትም ልማቱን የማስፋትና የመስኖ ግድቦችን የመገንባት ስራም በመከናወን ላይ መሆኑን የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ገልጿል።

በሚኒስቴሩ የጥናትና ዲዛይን ዳይሬክተር ኢንጂነር እንግዳሰው ዘሪሁን ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ መንግስት በመስኖ ልማት የያዘውን ግብ ለማሳካት የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ተናግረዋል።

የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ከሚደረገው ጥረት ባሻገር አዳዲስ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ጥናትና ዲዛይን እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

በ2014 በጀት ዓመት 520 ሚሊዮን ብር በመመደብ በ23 ፕሮጀክቶች ላይ የአዋጭነት ጥናትና የዲዛይን ስራ እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል።

የዲዛይን ጥናት እየተተገበረላቸው የሚገኙት ፕሮጀክቶች ትላልቅና መካከለኛ ግድቦች እንዲሁም የወንዝ መቀልበሻዎችን ያካተቱ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

ፕሮጀክቶቹ ሁሉንም ክልሎች ያካተቱ ስለመሆናቸውም ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት።

የአዋጭነት ጥናትና ዲዛይን እየተደረገላቸው ከሚገኙ የመስኖ ፕሮጀክቶች መካከል የተወሰኑት በፀጥታ ችግር ቢስተጓጎሉም በተቻለ መጠን በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ በልዩ ትኩረት ይሰራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም