የጅማ ዩኒቨርሲቲ ''ካባስ 6800'' የተሰኘ የቫይረስ መመርመሪያ ማሽን በስጦታ አገኘ

102

ጅማ፤ ግንቦት 15. 2014 (ኢዜአ)-የጅማ ዩኒቨርስቲ ''ካባስ 6800'' የተሰኘ የቫይረስ መመርመሪያ ማሽን ''ሮች" ከተሰኘ የጀርመን ኩባንያ አገኘ።

ማሽኑ  የማህጸን ካንሰርና የኩላሊት ንቅለ ተከላ የተሰራላቸው፣ የጉበትና የቲቢ በሽታን ጨምሮ የተለያዩ የቫይረስ በሽታዎችን ለማከም የሚያስችል መሆኑ ተመላክቷል።

የጅማ ዩኒቨርሲቲ ጤና ኢንስቲትዩት ክሊኒካል ዳይሬክተር ዶክተር ፈቲያ አወል በርክክብ ሥነ ሥርዓቱ ላይ  እንዳሉት ከዚህ በፊት በርካታ ህሙማን በመመርመሪያ ማሽን እጥረት ምክንያት ሪፈር ይደረጉ እንደነበር አስታውሰዋል።

ማሽኑ የተለያዩ የህክምና ችግሮችን መፍታት የሚችል መሆኑን ጠቁመው፤ የህሙማንን እንግልት የሚያስቀርና የምርመራ ስራን የሚያቀላጥፍ ይሆናል ብለዋል፡፡

ለተደረገው ድጋፍ  የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትንና ''ሮች'' የተሰኘውን ኩባንያ አመስግነዋል፡፡

በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና እንስቲትዩት የብሔራዊ ላቦራቶሪ አቅም ግንባታ አማካሪ አቶ ጎንፋ አያና በበኩላቸው የጅማ ዩኒቨርሲቲ ጤና ኢንስቲትዩት በርካታ ተገልጋዮችን ተደራሽ የሚያደርግ ተቋም መሆኑን ጠቁመው፤ የማሽኑ መገኘት  ለኢንስቲትዩቱ ስራ ጉልህ ሚና አለው ብለዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ አቅሙን እያጎለበተ መምጣቱን ጠቁመው፤ ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚያገልግል በመሆኑ የተሟላ አገልግሎት መስጠት እንዲችል አስፈላጊ ቁሳቁሶች እንደሚሟሉለት ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ሳይንስ ኢንስቲትዩት የላብራቶሪ ባለሞያ አቶ ፈይሳ ጫላ ''ካባስ 6800'' የተሰኘው ማሽን በጀርመን ሀገር በ2021 ተመርቶ የተዋወቀ መሆኑን ገልጸው፣ በሰዓት 864 ውጤቶችን መስራት የሚችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ማሽኑ  የካንሰር፣ የጉበት፣ የቲቢና መሰል የቫይረስ በሽታዎችን የሚመረምር ነው ብለዋል፡፡

የጀርመኑ ''ሮች'' ኩባንያ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር  በ2019 ለጤና ኢንስቲትዩቱ ተመሳሳይ የቫይረስ መመርመርያ ማሽን ማበርከቱ  በርክክቡ ወቅት ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም