የጎንደር ዩንቨርሲቲ ሀገር አቀፍ የምርምር ጉባኤ ሊያካሂድ ነው

87

ጎንደር ግንቦት 16/2014 (ኢዜአ) የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከ120 በላይ የጥናትና ምርምር ውጤቶችን ጨምሮ ልዩ ልዩ የፈጠራ ቴክኖሎጂዎች የሚቀርቡበት 30ኛውን ሀገር አቀፍ የምርምር ጉባኤ በነገው እለት እንደሚያካሂድ አስታወቀ፡፡

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ቢኒያም ጫቅሉ ለኢዜአ እንደገለጹት ጉባኤው ''የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ለማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት፣ ለመልሶ ግንባታና እድገት'' በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄድ ነው፡፡

ጉባኤው በተለይ በአማራና አፋር ክልሎች በአሸባሪው የህወሃት ቡድን ወረራ የደረሱ ጉዳቶችን መልሶ መገንባትበሚቻልበት ሁኔታ ላይ እንደሚመክር ተናግረዋል፡፡

የምርምር ውጤቶች፤ የማህብረሰብ አገልግሎትና የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ለክልሎቹ መልሶ ግንባታና የልማት ስራ በሚኖራቸው ሚና ላይ ሰፊ ምክክር በማድረግ ጉባኤው አቅጣጫ ያስቀምጣል ብለዋል።

በጉባኤው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከአማራ ዩኒቨርሰቲዎች ፎረምና ከሰመራ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመቀናጀት በሁለቱ ክልሎች የደረሰውን ጉዳት የሚያሳይ የምርምር ውጤትን ይፋ እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡

ከነገ ጀምሮ ለሶስት ቀናት በሚካሄደው የምርምር ጉባኤ ላይ በዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ ተመራማሪዎች የተዘጋጁ ከ100 በላይ ሀገር አቀፍ የምርምር ስራዎች እንደሚቀርቡ ተናግረዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲውና በአካባቢው በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች የተዘጋጁ ከ20 በላይ አዳዲስ የፈጠራ ቴክኖሎጂ ውጤቶች በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ በተዘጋጀው ኤግዚቢሽን ላይ ለእይታ እንደሚቀርቡ አስረድተዋል፡፡

ለሶስት ተከታታይ ቀናት በሚካሄደው ሀገር አቀፍ የምርምር ጉባኤ ላይ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የስራ አመራር ቦርድ አባላት፣ ተመራማሪዎች፣ መምህራንና ተማሪዎች እንደሚሳተፉ ተመላክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም