የጽንፈኝነትና አክራሪነት አስተሳሰብ አለመክሰም ለግጭቶች መከሰት መንስኤ ሆኗል - ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ

154

አደስ አበባ፤ ግንቦት 15 ቀን 2014 (ኢዜአ) የጽንፈኝነትና አክራሪነት አስተሳሰብ አለመክሰም ለግጭቶች መከሰት መንስኤ ሆኗል ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ኃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ገለጹ።

የኢትዮጵያውያንን ትስስር በመበጣጠስና ህዝቡን በመከፋፈል ኢትዮጵያን ለማዳከም ያልተሸረበ ሴራ አልነበረም።

በተለይ ባለፉት አራት ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ ብሄርን፣ ሀይማኖትን፣ ወሰንንና ሌሎች ማንነቶችን ሽፋን በማድረግ የተከሰቱ ግጭቶች በርካታ ናቸው።

ግጭቶቹን ተከትሎም የሰው ህይወት ጠፍቷል፤ ብዙዎች ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፤ የግለሰብ፣ የህዝብና የመንግስት ንብረት ላይም ከፍተኛ ውድመት ደርሷል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ኃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ እነዚህ ግጭትች የውስጥና የውጪ ሀይሎች ተጣምረው የፈጠሯቸው ናቸው ይላሉ።

በሕዝብ ግፊትና ጫና የመጣውን ለውጥ መቀበል የተሳናቸው አካላት ለውጡን ለማደናቀፍ ግጭቶችን ሲጠነስሱ፣ በገንዘብ ሲደግፉና ለጥፋት የመለመሏቸውን ሀይሎች ሲሰማሩ እንደነበረም ያነሳሉ።

ጸረ ለውጥ ሀይሎች ከኢትዮጵያ ሕዝብ ያለአግባብ ያጋበሱትን ሀብት መልሶ ለማግኘትና ስልጣንን ዳግም ለመቆጣጠር ብዙ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ያለውን ያልዳበረ የፖለቲካ ባህል እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅመውበታልም ብለዋል።

ከሁሉም በላይ በሕዝቦች መካከል ለዘመናት ሲዘራ የነበረውን የጥላቻና በጥርጣሬ የመተያየት ትርክት ለግጭት መፍጠሪያነት ማዋላቸውንም ነው የገለጹት።

የጽንፈኝነትና የአክራሪነት አስተሳሰብ አለመክሰሙ ግጭቶቹ እንዲባበሱ ካደረጉ ክስተቶች መካከል ዋነኛው መሆኑን ገልጸው ለውጡን ማደናቀፍ የሚፈልጉ አካላት አዝማሚያውን ለግጭት መፍጠሪያና ማባባሻነት ተጠቅመውበታል ብለዋል።

ግጭት ጠማቂዎቹ የአገር ውስጥ ጸረ ለውጥ ሀይሎች ብቻ አለመሆናቸውን የጠቀሱት ዶክተር ቢቂላ የኢትዮጵያን መፍረስ የሚፈልጉ የውጪ ሀይሎች ተሳትፎም ነበረበት ብለዋል።

ኢትዮጵያ የራሷን ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች በራሷ አቅም የማትፈታ ደካማ አገር እንድትሆን ቀን ከሌሊት ሲሰሩ የነበሩ የውጭ አካላት መኖራቸውን በመጥቀስ።

በተለይም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያላት የጂኦ ፖለቲካዊ ሁኔታ የማያስደስታቸው አካላት መኖራቸውንም ተናግረዋል።

የውስጥና የውጭ ሀይሎች የተናበበ ሴራ ኢትዮጵያውያንን እንደ ሕዝብ የጎዳ መሆኑን ጠቅሰው ንጹሓን ዜጎች መገደላቸውን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን፣ ሀብት ንብረታቸው መውደሙን ገልጸዋል።

ነገር ግን ጸረ ለውጥ ሀይሉ እንዳሰበው ኢትዮጵያን ማፍረስ እንዳልቻለና ኢትዮጵያ በዜጎቿ መሰዋዕትነት የምትጠበቅ አገር መሆኗ ተረጋግጧል ብለዋል።

መንግስት የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ እንዲሁም አገርን ለማስቀጠል የተቀናጀ ስራ መስራቱን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ጠላቶች የሁል ጊዜ ፍላጎታቸው የህዝብን አንድነት በመሸርሸር በጥርጣሬ እንዲተያይ ማድረግና በሂደትም አገርን ማፍረስ መሆኑን በመገንዘግ ኢትዮጵያውያን ከመንግስት ጋር በመሆን የጋራ ቤታቸውን መጠበቅ ይገባቸዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም