ለኢንተርፕራይዞች እና ለግሉ ኢንዱስትሪ ማነቆ የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት አመራሩ ሊሰራ እንደሚገባ ተጠቆመ

63

ሀዋሳ፤ ግንቦት 15 ቀን 2014 (ኢዜአ) ለኢንተርፕራይዞች እና ለግሉ ኢንዱስትሪ ማነቆ የሆኑ ተግዳራቶችን ለመፍታት ሊሰሩ እንደሚገባ የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ አባል እና የሲዳማ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብርሃም ማርሻሎ ተናገሩ።

በሲዳማ ክልል የመጀመሪያ ዙር ስልጠና ላይ ተሳታፊ የሆኑ 1 ሺህ 280 ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች በክልሉ የሚገኙ የኢንዲስትሪ ተቋማትን እና ሞዴል ኢንተርፕራይዞችን ዛሬ ተዘዋውረው ጎበኝተዋል።

ሀብት እየፈጠሩ ያሉ ማህበራት ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር እንዲችሉ ከአመራር ሥርዓቱ ጋር ለማቀናጀት ታስቦ ጉብኝቱ መዘጋጀቱን አቶ አብርሃም ማርሻሎ አስታውቀዋል።

ጉብኝቱም አመራሩ በተግባር ከሚያቸው የልማት ውጤቶች ልምድ በመቅሰምና በመቀመር ለኢንዱስትሪው ዘርፍ  በቂ  ግብዓቶች እንዲቀርብ  የአመራር ሚናውን እንዲጫወት የሚያደርግ መሆኑን አመልክተዋል።

አንቀሳቃሾች ውጤታማ እንዲሆኑ እያጋጠማቸው ያለው የግብዓት እጥረት ሊፈታ ይገባል ያሉት ኃላፊው፤ የግብዓት እጥረቱ  ከውጭ የሚገባውን ምርት በሀገር ውሰጥ ለመተካትና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የተጀመረውን ጥረት እንዳያስተጋጉል ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በክልሉ በእንስሳት ሀብት ልማት የተሰማሩ ማህበራት የወተት ምርት  ለሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ ለይርጋለም የተቀናጀ አግሮ እንዱስትሪ ፓርክ እና ለህብረተሰቡ በማቅረብ ሀብት እያፈሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኢንተርፕራይዞችን በመደገፍ ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች እንዲሸጋገሩ መስራት እንደሚገባ አመላክተዋል።

አሁን ላይ ከጥሬ ዕቃ አቅርቦት ጋር ተያይዞ ኢንዱስትሪዎች እያጋጠማቸው ያለው ተግዳሮት በተለይ ከውጭ የሚገባውን ምርት በሀገር ውሰጥ ለመተካት የሚደረገውን ጥረት እንዳያስተጓጉል የሁሉንም ርብርብ እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።

አመራሩ ለግሉ ኢንዱስትሪ ማነቆ የሆኑ ችግሮችን ትኩረት ሰጥቶ በመፍታት አርሶ አደሩንና ወጣቶችን ተጠቃሚ ማድረግ እንዳለበት  አሳስበዋል።

በአመራሮቹ ከተጎበኙ ተቋማት መካከል የአዳሬ የዶሮ እርባታ ማዕከል ተጠባባቂ ሥራ አስኪያጅ አቶ ግዛቸው ታደሰ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት ማዕከሉ የአንድ ቀን ጫጩቶች ለማስፈልፈል የተቋቋመ መሆኑን ገልጸው በ21 ቀን ከ130 ሺህ እስከ 150 ሺህ ጫጩቶችን የማስፈልፈል አቅም  እንዳለው ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት 10 ሺህ እንቁላል ጣይና የሥጋ ዶሮዎችን በዘመናዊ መንገድ እያረባ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

ካለፈው ታህሳስ ወር ወዲህ ብቻ 56 ሺህ የአንድ ቀን ጫጩቶች በመፈልፈል ለሲዳማ፣ደቡብና ኦሮሚያ ክልል ለሚገኙ ተጠቃሚዎች ማሰራጨቱን አመልክተዋል።

በ2015 ዓ.ም ማዕከሉ በዓመት 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ጫጩቶችን በመፈልፈል ለማሰራጨት ማቀዱን ተጠባባቂ ሥራ እስኪያጁ አስታውቀዋል።  

ከጉብኝቱ ተሳታፊ አመራሮች መካከል የይርጋለም ከተማ አስተዳደር እና የሲዳማ ክልል አመራር የሆኑት አቶ ሳሙዔል ቦጋለና ወይዘሮ ፀጋነሽ ሀጎስ በሰጡት አስተያየት ከስልጠናው በተጓዳኝ ያደረጉት የልማት ጉብኝት በተለይ በትንሽ ቦታ ላይ ተደራጅቶ በመስራት ሀብት ማፍራት እንደሚቻል ግንዛቤ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

ይህንን ልምድና ተሞክሮ በመቀመር ወደ አካባቢያቸው ለማስፋፋት መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።

አመራሮቹ  በአራት ቡድን ተከፍለው ከጎብኟቸው   ተቋማት መካከል  ታቦር ሴራሚክ ፋብሪካ ፣የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ፣  አዳሬ የዶሮ እርባታ ማዕከል፣አዳሬ እንስሳት እርባታና መኖ ልማት ህብረት ስራ ዩኒየን፣ ይርጋለም የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ይገኙበታል።